Search

ለኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ምኅዳር አዲስ ምዕራፍ የከፈተው ስትራቴጂ

ሰኞ ታኅሣሥ 13, 2018 49

"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እንድታድግ የሚያስችላት እና ብልፅግናዋን ዕውን ለማድረግ የላቀ ሚና እንደሚኖረው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል አማካሪ የሆኑት ሚሪያም አሊ ይገልጻሉ።
ስትራቴጂው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን የጠቀሱት አማካሪዋ፤ ይህም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ስትራቴጂው ይፋ በተደረገበት ወቅት ተናግረዋል።
ዓለም በፍጥነት እየተንቀሳቀሰችና ሰው ሠራሽ አስተውሎትም (AI) ዓለምን እየቀየረ መሆኑን ያነሱት አማካሪዋ፤ ከዚህ ፈጣን ዓለም ጋር ለመራመድ ዜጎች ቀልጣፋ፣ ቀላልና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ስትራቴጂውን በሥራ ላይ ማዋል መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል።
ሁሉም ዘርፎች በዲጂታል መሠረተ ልማት ካልተደገፉ ተወዳዳሪ ሆነው መውጣት እንደማይችሉም ያብራራሉ።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካታች እና በግልጽ ዓላማ የሚመራ ስትራቴጂ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የተጣለውን መሠረት ማስፋፋት ዋነኛ ግቡ እንደሆነም ይገልጻሉ።
ስትራቴጂው ከሙከራ ፕሮጀክቶች ወደ ሀገር አቀፍ ሥርዓቶች፣ ከተከፋፈሉ አሠራሮች ደግሞ ወደ ተቀናጁ አገልግሎቶች የሚሸጋገርበት የውጤት ማሳያ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
ዲጂታል አገልግሎቶችን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የሚተጋው ይህ ስትራቴጂ፤ ሉዓላዊ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥርዓት ያለው፣ መሠረቱ ኢትዮጵያዊ በሆነ ፈጠራ ላይ የተገነባና መላውን ኢኮኖሚ የሚለውጥ እንደሆነም አማካሪዋ አስረድተዋል።
እንደ አማካሪዋ ገለጻ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አራት ዋና ዋና ግልጽ ዓላማዎች አሉት። እነሱም ሰዎችንና ተቋማትን ማብቃት፣ ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ አካታች ዲጂታል የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ እና ኢትዮጵያን ዋነኛ የዲጂታል ኢኮኖሚ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ ናቸው።
እነዚህ አራት ዓላማዎች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት መለኪያዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አማካሪዋ፤ የኃይል መሠረተ ልማት፣ ኢንተርኔት እና ተዓማኒነት ዓላማዎቹን ለማሳካት የሚረዱ መሠረቶች እንደሆኑም ሚሪያም አሊ ይገልጻሉ።
 
በለሚ ታደሰ