በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሳይበር ደኅንነት ለሀገሪቱ የዲጂታል ዕድገት እንደ አንድ መሠረታዊ መሠረት ሆኖ መለየቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ኢንዴክስ ከነበረበት 34 በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ አማካኝነት አሁን ላይ ወደ 76.3 ከፍ ማለቱን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት ለኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት፣ ለፋይዳ እና ለኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት የሚያገለግለው የሕዝብ ቁልፍ መሠረተ ልማት (PKI) ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው፤ በዘርፉ ባለሙያዎች በከፍተኛ ትምህርት ከማስመረቅ ባለፈ በርካታ ታዳጊዎች የሳይበር ደኅንነት ሥልጠና ማግኘታቸውንም አስረድተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ደግሞ የመንግሥት አገልግሎት፣ የትምህርት፣ ግብርና እና ጤና ዘርፎች የሚጠቀሙት መሠረተ ልማት በቁልፍ ተቋማት ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን የሚበግር ሊሆን እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
የሕዝብ ቁልፍ መሠረተ ልማትን ለሌሎች ዘርፎች ተደራሽ የማድረግ እና የማይበገር የዲጂታል ‘የሲግኔቸር’ (የማረጋገጫ) ሥርዓት የመዘርጋት ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።
ስትራቴጂው የግል ተቋማት በሳይበር ደኅንነት ሥራዎች ላይ በጥልቀት እንዲገቡና በዘርፉ በስፋት እንዲሠሩ የሚያስችል ዕድልን ይዞ የመጣ መሆኑንም አብራርተዋል።
በ2030 የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነት አቅም በእጅጉ በማሳደግ ኢትዮጵያን በዘርፉ የዓለም አቀፍ ሞዴል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራም ዋና ዳይሬክተሯ አረጋግጠዋል።
በላሉ ኢላታ