ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በእንጦጦ ፓርክ ግንባታ ላይ ጉልህ አሻራ ያሳረፉና ለሥራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር ያስመሰከሩ ሦስት ብርቱ ሴቶችን አስደናቂ የፈጠራ ሥራ በማንሳት ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ እነዚህ ሴቶች የሠሯቸው ሥራዎች ከገንዘብ ትርፍ ይልቅ ለትውልድ የሚሻገር ታሪክን እና ሀገራዊ እሴትን ማዕከል ያደረጉ ናቸው።
የመጀመሪያዋ የዞማ ሙዚየም (Zoma Museum) መሥራችና ባለቤት መስከረም አሰገድ ስትሆን፣ እንደ ዲዛይነርና አናጺ በመሆን ላለፉት 6 ዓመታት ያለ ዕረፍት በእንጦጦ ላይ በቁርጠኝነት የሠራች ባለሙያ ናት።

መስከረም በጭቃና በሀገር በቀል ጥበብ የሚሠሩ ግንባታዎች ላይ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላት ሲሆን፣ በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ የሚታዩት አስደማሚ የድንጋይና የጭቃ ሕንጻዎች እንዲሁም የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራዎች የእርሷ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው።
የሥራዋ ውጤት ቁሳዊ ጥቅምን ሳይሆን ታሪክን ለትውልድ ማሸጋገርን ዓላማ ያደረገ በመሆኑ፣ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ሲጎበኝ የሚኖር ትልቅ ሀገራዊ እሴት እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በተለይም በእንጦጦ ላይ የሚገኘውን ገደላማ ስፍራ ሙሉ ለሙሉ በሀገር በቀል ዕፅዋት እንዲሸፈን በማድረግ ረገድ ሰፊ ሥራ አከናውናለች።
ሁለተኛዋ በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ የኢትዮጵያን ባህላዊ ቅርሶች በጥበብ በመግለጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያበረከተችው የባህላዊ ቅርሶች እና ጥበብ ባለሙያዋ ሳባ አለነ ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ሳባ በምትሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የልቧን ግዝፈትና ቅንነት ማንጸባረቅ የቻለች ድንቅ እንስት ናት።
የሳባ ሥራዎች የኢትዮጵያን የጥበብ ታሪክና ባህል ለዓለም የሚያስተዋውቁ አስደማሚ ውጤቶች እያሳዩ መሆናቸውን አድንቀዋል።

ሦስተኛዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀዋ የሰርከስ ጥበብ ባለሙያ እና አሰልጣኝ ሶስና ወጋየሁ ናት።

"ኢትዮ-ሰላም ሰርከስ" የተሰኘው ተቋም መሥራች እና መሪ የሆነችው ሶስና፣ ታዳጊዎችን እና ወጣቶችን በማሰልጠን በዓለም መድረክ የኢትዮጵያውያንን ብቃት የምታሳይ ባለሙያ ናት።
ይህ የሰርከስ ጥበብ ኢትዮጵያ እንግዶቿን ስትቀበል የምታቀርበው እና እነርሱም በእጅጉ የሚደመሙበት መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያወሱት።
ሶስና እንጦጦ ላይ እየሠራችው ያለው ሥራ ለሀገሯ ያላትን ፍቅር የሚገልጽ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
እነዚህ ሦስት እንስቶች በእንጦጦ ፓርክ ግንባታ ላይ ያሳረፏቸው ድንቅ አሻራዎች፣ በተለይም ወጣቶችን አቅፎ የያዘው የሰርከስ ሥራ ከባህልና ቅርስ ጋር ተናቦ መሠራቱ ከመዝናኛነት ባለፈ ታሪካዊ ትርጉም እንዲኖረው አድርጎታል።
እነዚህ የዲዛይን፣ የባህልና የሰርከስ ሥራዎች ተቀናጅተው ሲታዩ ለሀገር ትልቅ ፋይዳ አላቸው።
በተፈጥሮ በተዋበው እንጦጦ በእግር እየተጓዙ እነዚህን የሥራ ውጤቶች መመልከት በአካልና በአእምሮ ላይ ከሚፈጥረው እርካታ ባሻገር፣ በዜጎች ዘንድ የሀገር ፍቅር እና የአርበኝነት ስሜት እንዲጎለብት የማድረግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉትም፣ የእነዚህ ጠንካራ እንስቶች ሥራ ትውልድን የሚሻገር እና ኢትዮጵያ ምን ያክል የታደለች ሀገር እንደሆነች የሚያሳይ የተግባር አርበኝነት (Patriotism) ማሳያ ነው።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ