Search

ከካሜራ ባለሙያነት እስከ አውሮፕላን አብራሪነት፡ የዳንኤል አስገራሚ ጉዞ

ዓርብ ሚያዝያ 09, 2018 270

በጣሊያን ሜሲና ከተማ ተወልዶ ያደገው በአባቱ ጣሊያናዊ፣ በእናቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነው ዳንኤል ማንቲንዮ በልቡ ውስጥ ትልቅ ህልም ሰንቆ አደገ።

በልጅነቱ ከእናቱ ጋር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እናት ሀገሩ በሚመላለስበት ወቅት በአውሮፕላን አብራሪዎቹ ግርማ ሞገስና ዩኒፎርም ይማረክ የነበረው ዳንኤል፣ ከአድማስ ባሻገር ለምትገኝ ሀገሩ ካለው ጥልቅ ናፍቆት ጋር የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደማቅ አረንጓዴ ልብስ ለብሶ ሰማዩን የመሰንጠቅ ህልም አብሮት ተጓዘ።

ዛሬ ህልም በፅናትና በትጋት እውን ሆኖ፣ ረዳት አብራሪ ዳንኤል ማንቲንዮ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ በኩራት ከፍ ለማድረግ በቅቷል።

የዚህ አስደናቂ ጉዞ መነሻ ዳንኤል ገና 13 ዓመት ታዳጊ እያለ ሲሆን፣ እናቱ በልጇ የቋንቋ ችሎታ ተደንቃ "ተርጓሚ ወይም ዶክተር ቢሆን" የሚል ምኞት ቢኖራትም፣ በአንድ አጋጣሚ ያገኘቻቸው ፕሮፌሰር የጠየቁት "ወደፊት ምን መሆን ትፈልጋለህ?" የሚል ጥያቄ ግን የሕይወቱን አቅጣጫ ቀየረው። ዳንኤል ሳይወላውል "የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪ!" ሲል የሰጠው መልስ ለእናቱም ሆነ ለፕሮፌሰሯ አስገራሚ ነበር።

ይህንን ህልም እውን ለማድረግ 13 ዓመት ዕድሜ ቤተሰብንና ጓደኛን ጥሎ መሰደድ ከባድ ቢሆንም፣ ዳንኤል ግን የልቡን ምሪት ተከትሎ በጣሊያን ከቤተሰቡ ተለይቶ የአምስት ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ጀመረ።

ትምህርቱ አዲስና ከባድ፣ ቋንቋውና ጫናው ደግሞ ክፉኛ በፈተኑት በዚያ ወቅት፣ ግራ ገብቶት የሚያለቅስባቸውና ጓደኞቹ እንኳ እርዳታ የሚነፍጉት ቀናት ቢኖሩም ተስፋ ሳይቆርጥ ወደ ፈጣሪ በመጸለይ በትምህርቱ አንቱታን አተረፈ።

 ሆኖም ሌላ ፈተና ገጠመው፤ በበረራ ትምህርቱ ወቅት በነበረ የበጀት እጥረትና በአንድ ባልተሳካ የአውሮፕላን ማረፍ ሙከራ ምክንያት ከትምህርቱ እንዲቀነስ ተደረገ።

ቀን ለዳንኤል ተስፋው የጨለመ ቢመስልም፣ በፅናት ተመልሶ በመግባት የፕራይቬት ፓይለት ፈቃዱን (PPL) በብቃት ተቀበለ፤ ለመጀመሪያ ጊዜም አውሮፕላን ለብቻው አብርሮ ሲያርፍ የደስታ እንባው በጉንጮቹ ላይ ይፈስ ነበር።

ዳንኤል ጣሊያን ሆኖ ስለ እናት ሀገሩ የሚነገሩ የተዛቡ ምስሎችን ለመቀየር ይተጋ ስለነበር፣ "ኢትዮጵያ ውስጥ አውሮፕላን አለ እንዴ?" ብለው ለሚሳለቁበት ጓደኞቹ ምላሽ ለመስጠት በአሁኑ ወቅት 243 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው "Ethiopian Airlines Fan Page" የሚል የፌስቡክ ገፅ በመክፈት ስለ አየር መንገዱ ስኬትና ዘመናዊነት በማስተዋወቅ አመለካከታቸውን ቀይሯል።

ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ ወደ አቪዬሽን አካዳሚ ለመግባት ያደረገው የመጀመሪያ ሙከራ ባይሳካም ተስፋ ቆርጦ ወደ ጣሊያን ከመመለስ ይልቅ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ተቀጥሮ አገለገለ፡፡ እንዲሁም በቤተክርስቲያን የካሜራ ባለሙያና ኤዲተር ሆኖ በማገልገል ህልሙን በፅናት ጠበቀ።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በሮች ተከፈቱለትና ስልጠናውን በከፍተኛ ዲሲፕሊን አጠናቅቆ 2025 በረዳት አብራሪነት ተመረቀ።

ዛሬ ዳንኤል ያንን ለዓመታት የተመኘውን አረንጓዴ ዩኒፎርም ለብሶ የሀገሩ አምባሳደር በመሆን ዓለምን ለመዞር የተዘጋጀ ሲሆን፣ "ህልም ካላችሁ ተስፋ አትቁረጡ" በማለት ለኢትዮጵያ ወጣቶች የፅናት ተምሳሌት ሆኗል።