የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳውዲ አረቢያ አምስተኛ መዳረሻው ወደ ሆነችው ጂዛን አዲስ የመንገደኞች አገልግሎት እንደሚጀምር አሳውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም በሳውዲ አረቢያ አራት መዳረሻዎች የነበሩት ሲሆን፤ እነዚህም ጅዳ፣ ደምማም፣ ሪያድ እና መዲና ናቸው።
አሁን ደግሞ ከእነዚህ በተጨማሪ ወደ ውቧ እና የዓለም ቅንጡ ሀብታሞች ለመዝናናት እንዲሁም ለመኖር ወደሚመርጧት ጂዛን በፈረንጆቹ 2026 መዳረሻውን ለማድረግ ማቀዱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታውቋል።

የጂዛን ከተማ በሳውዲ አረቢያ ደቡብ ምዕራብ፣ በቀይ ባህር ዳርቻ የምትገኝ ስትሆን፤ በአሁኑ ወቅት በሳውዲ አረቢያ የ2030 ራዕይ መሰረት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ እያመጣች ያለች ናት።
የከተማዋ ኢኮኖሚ ከዚህ ቀደም በግብርና እና በባሕር ሐብት ላይ ተመስርቶ የቆየ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ግዙፍ የኢንዱስትሪ እና የዓለም አቀፍ ንግድ ማዕከልነት እየተቀየረች ትገኛለች።
ጂዛን በተፈጥሮአዊ ውበቷ፣ በባህሏ እንዲሁም በታሪካዊ ቦታዎቿ የምትታወቅ አስደናቂ ከተማ መሆኗ የሚነገርላት ናት።

ይህች ተፈጥሮ ድንቅ አድርጎ የፈጠራት በደሴቶች የተከበበች ከተማ “የደቡብ እንቁ” በሚል ቅፅል ስም ትታወቃለች።
ጂዛን የግብርና እምብርት ናትም ይባልላታል፤ እንደ ማንጎ፣ በለስ፣ ፓፓያ እንዲሁም ቡናን በጥራት ታመርታለች።
ይህቺው ድንቅ ከተማ የባሕር ወደብ ባለቤትም ናት። የጂዛን ወደብ በቀይ ባሕር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከአፍሪካ፣ ከእስያ እና ከአውሮፓ ጋር ለሚደረግ የንግድ ልውውጥ ዋና በር በመሆን ያገለግላል።
ጂዛን በበርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመቱ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሚከናወኑባት ከተማ ስትሆን፤ በታዳሽ ኃይል፣ በቱሪዝም፣ በግብርና እና በዓሣ ምርት ጎልታ ትጠቀሳለች።
ጂዛን በተራሮቿ ላይ ልዩ መዓዛ ያለው “ኻውላኒ” (Khawlani) የተሰኘ ቡና የምታበቅል ሲሆን፤ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ እና ኢኮኖሚያዊ ገቢም የሚያስገኝላት ነው።
በጂዛን ከሚገኙ ውብ የቱሪስት መስህቦች መካከል የፋራሳን ደሴቶች ተጠቃሽ ናቸው፤ በንፁህ ነጭ አሸዋማ የባሕር ዳርቻዎች የተከበቡ ከ80 በላይ ደሴቶች የሚገኙባት ይህቺ ከተማ ጥልቀት በሌለው ሰማያዊ ባሕሯም ትታወቃለች።

በደሴቶቹ ላይ ታሪካዊ እና ጥንታዊ የአሸዋ ድንጋይ ቤቶች እና ጥንታዊ የኦቶማን ምሽጎችም ይገኛሉ።
በእነዚህ ስፍራዎች ከአውሮፓ የሚፈልሱ በርካታ የእፅዋት ዝርያዎችን እየተመለከቱ መዋኘት፣ እንዲሁም በባሕር ዳርቻዎቹ መንሸራሸር የተለመደ ነው።
በቀለማት ያሸበረቁ የባሕር ውስጥ ፍጥረታት የሚገኙበትን ባሕር በርካቶች ለመዝናናት ይመርጡታል፤ ስፍራው የቀይ ባሕር ዳርቻ በመሆኑ፣ ትኩስ ዓሣ እና ሌሎች የባሕር ምግቦች በብዛት ይገኙበታል።

ከባህር ጠለል በላይ በ2000 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኙት የፋይፋ ተራሮቿም “የጎረቤት ደመናዎች” የሚል ቅፅል ስያሜ አላቸው።
ይህ ስፍራ በሳውዲ አረቢያ ካሉ ደረቃማ ቦታዎች በተለየ መልኩ ተራሮቹ አረንጓዴ እና በእርሻ የተሞሉ ናቸው፤ ዓመቱን ሙሉ ነፋሻ እና ደስ የሚል የአየር ፀባይ ያላቸው አካባቢዎች በመሆናቸው፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ጨምሮ የዓለማችን እውቅ እና ሀብታም ሰዎች ለኑሮ እንዲሁም ለመዝናናት ይመርጡታል።

የጂዛን የቅርስ መንደር ደግሞ የአካባቢውን ታሪክ እና ባህል በአንድ ስፍራ ለመመልከት ተመራጭ ነው።
በዚህ መንደር በሚገኙ ባህላዊ ቤቶች የጂዛን ታዋቂ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ይገኙባቸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች የሚለብሷቸው ባህላዊ አልባሳት እና የቤት ቁሳቁስም የተለዩ መስህቦችን ይፈጥራሉ።
የአል ዶሳሪያ ምሽግ በጂዛን ከተማ ከፍተኛ ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የከተማዋን እና የቀይ ባህርን ውብ እይታ ለመቃኘት የሚያስችል ተመራጭ ስፍራ ነው። በመሆኑም ታሪካዊ ቦታን መጎብኘት የሚወዱ ሰዎች ይህን ድንቅ ስፍራ እንዲጎበኙት ይመከራል።

ከጂዛን ከተማ ጎብኚዎች አብዛኛዎቹ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሲሆኑ፤ በተለይ ከሪያድ፣ ከጅዳ እና ከደምማም የሚመጡ ዜጎች ይበረክታሉ።
የጎረቤት ሀገራት የመን እና ኩዌት ጎብኚዎችም በተለይ በክረምት ወቅት ይህን ስፍራ ያዘወትሩታል።
ሳውዲ አረቢያ የቱሪስት ቪዛ መስጠት ከጀመረች በኋላ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በዚህም ከአውሮፓ በተለይ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ እንዲሁም ቻይና እና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ ከምስራቅ እስያ ለሥራ እና ለጉብኝት ያዘወትሯታል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream #EthiopianAirlines #Jizan