Search

የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ እንዲፀድቅ ተወሰነ

ዓርብ ታኅሣሥ 17, 2018 362

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በሁሉም መስክ የሥራ ፈጠራ ባህልን በማስረጽ ቀጣይነት ያለው እና ፈጣን ዕድገትን ዕውን ለማድረግ ኢንተርፕረነርሽፕ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዛሬው ዕለት የኢፌዲሪ ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲን በተመለከተ ከዲጂታል ካውንስል አባላት ጋር በበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።

ይህን ተከትሎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፖሊሲ በዋናነት ሁሉን አቀፍ እና አካታች ሀገራዊ የኢንተርፕረነርሽፕ ንቅናቄን በማቀጣጠል ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር ተጣጣሚ በሆነ መልኩ የዲጂታል ሥራ ፈጠራንና ተወዳዳሪነትን የሚያበረታታና የሚደግፍ ነው ብለዋል።

የፖሊሲ ማዕቀፉ ችግር ፈቺ ማህበረሰብን ለመገንባት፣ የፈጠራ ባህልን ለማጎልበት፣ እሴትን ለመጨመር እንዲሁም ምቹ ሥነምህዳርን ለመገንባት የሚያስችል የኢኮኖሚ ዕድገት ማዕቀፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሀገራችንን የኢንተርፕረነርሽፕ ሥነ-ምህዳርና የሥራ ፈጠራ ውጥኖችን አቅጣጫ በመስጠት የመምራት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በተለይ የኢንተርፕረነርሽፕ ስነ-ምህዳሩን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የጋራ አመለካከቶችን፣ እምነቶችንንና ባህሪያትን ለማጎልበት በዕጅጉ እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።

የልማት ፖሊሲው የታለመለትን ውጤት ማምጣት እንዲችል በፖሊሲው ትግበራ ወቅት የሚታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን በመለየት በየደረጃው ወጥና ጠንካራ የክትትል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ከዲጂታል ካውንስሉ ጋር መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ እና ግብዓቶችን በመጨመር የልማት ፖሊሲ ሰነዱ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ እንዲፀድቅ የተወሰነ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #entrepreneurship #policy