Search

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እየገነባች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ቅዳሜ ታኅሣሥ 18, 2018 300

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እየገነባች እንደሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) 2025 ዐውደ ርዕይና ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላት አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም ከፍተኛ ተጎጂ እንደሆነችም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ተፈጥሮን መጠበቅ እና መንከባከብ የተሻለ ነገን ለትውልድ ለማሻገር ያስችላል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ተፈጥሮ ሲጎዳ የሰው ልጅ ከፍተኛና ዘርፈ ብዙ ችግርን ይጋፈጣል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገቧን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረገ ኢኮኖሚ በመገንባት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ተጨባጭ ሥራ በመሥራቷ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝታበታለች ተብሏል።
 
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ሥራ በትራንስፖርት ዘርፉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ናቸው።
በዘርፉ የአየር ብክለትን ለማስቀረት በተሠራ ሥራ የባቡር አገልግሎት ታዳሽ የኃይል ምንጭ እንዲጠቀም የተደረገበት እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በዘርፉ መሰማራት ትልቅ እርምጃ እንደሆነም ሚኒስትሩ አንስተዋል።
እንዲሁም አሮጌ መኪና ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የተደረገበት አሠራር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ብክለትን ለማስቀረት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ከ500 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።
 
በአቤል ሙሉጌታ