Search

የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ የሚጠይቀው የጋራ ጥረት

ቅዳሜ ታኅሣሥ 18, 2018 353

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ፣ ያለ ዘላቂ ሰላም የሚሳካ ዕድገትም ሆነ ልማት እንደማይኖር በተለያዩ መድረኮች ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የመደመር መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝና ለዚህም የዜጎች ሚና ወሳኝ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ማሳሰባቸውም ይታወሳል።
በሰላም ግንባታ ሒደት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ምሁር አቶ እያሱ ኃይለሚካኤል ናቸው።
አቶ እያሱ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በሐሳብ ላይ የተመረኮዘ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረግ ሕዝብን ከሰላም እጦትና እንግልት መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ልዩነቶችን በሰለጠነ አግባብና በሀገር በቀል የእርቅ ሥርዓቶች በመፍታት ችግሮችን ማስቀረት እንደሚቻል የገለጹት ምሁሩ፤ ይህም ዴሞክራሲንና ልማትን በዘላቂነት ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።
ሰላም ባለበት ልማት ይኖራል ያሉት አቶ እያሱ፤ ዘላቂ ሰላም ሲኖር ከፍተኛ የሆነ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በመግባባት ውስጥ ሀገራዊ የልማት ዕቅዶች በተሳካ ሁኔታ ይተገበራሉ የሚለውን እሳቤ በመያዝ፣ ለሀገራዊ መግባባትና ለሰላም ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
አስተማማኝ ዕድገትን ለማምጣት ዘላቂና አካታች ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት አቶ እያሱ፤ ሀገራዊ መግባባትን በመገንባት ሒደት ሁሉም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
 
በሜሮን ንብረት