የአማራ ክልል የ2018 ዓ.ም የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የንቅናቄ መድረክ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በኬሚሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፥ በክልሉ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ላለፉት 7 ዓመታት ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን አውስተዋል።
ይህም አፈርን ከመሸርሸር ታድጎ ለግብርና ምርታማነት ምቹ ምሕዳር በመፍጠር በምርት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት አስችሏል ብለዋል።

አሁን ያለውን የመሬት ሀብት በአግባቡ ተጠቅሞ ለትውልድ ለማስተላለፍ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ በዘንድሮው ዓመትም በክልሉ በስፋት እንደሚሠራበት ገልጸዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወቅት ብቻ ሕዝቡን በማሳተፍ ከ9 ሺህ በላይ በሚሆኑ ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ጠቅሰው፤ በንቅናቄው ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ፥ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለሁሉም የግብርና ሥራዎች መነሻ እና ማቀናጃ ነው ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በተፋሰስ ልማት ለክልሉ ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ የንቅቅናቄ መድረኩ በዞኑ መካሄዱ ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
የ2018 ዓ.ም የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በደቡብ ወሎ ዞን፣ አርጎባ ልዩ ወረዳ በነገው ዕለት በይፋ እንደሚጀመርም የቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበኩላቸው፥ በዞኑ ለተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የተሰጠው ትኩረት እና የአርሶ አደሩ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ይህም የአፈር ለምነትን አሻሽሎ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመግለፅ፤ በዘንድሮው ዓመትም የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣለን ብለዋል።

በክልላዊ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የንቅናቄ መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ
#EBC #ebcdotstream #AmharaRegion #naturalresource #management