Search

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የቅድመ-መከላከል እና የመሠረተ-ልማት ማሻሻያ ሥራዎች ተከናውነዋል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

ማክሰኞ ሰኔ 02, 2018 53

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ሰፊ የቅድመ-መከላከልና የመሠረተ-ልማት ማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በአገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ሥራ አስፈፃሚ ገበየሁ ሊካሳ (/) ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ያረጁ መስመሮችን የመተካት፣ አቅምን የማሳደግ እና አዳዲስ መሠረተ-ልማቶችን የመገንባት ሥራዎች በከፍተኛ ወጪ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኃይል መቆራረጥ በዕቅድ (ለጥገና እና ተከላ) እንዲሁም በድንገተኛ ብልሽት እና አደጋ ምክንያት እንደሚከሰት የጠቆሙት ሥራ አስፈፃሚው፣ ችግሩን ለመቅረፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ 62 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመካከለኛ መስመር ፍተሻ መደረጉን እና 67 ሺህ በላይ ትራንስፎርመሮች መመርመራቸውን አስረድተዋል።

በዚህም በኔትወርክ እና በትራንስፎርመሮች ላይ ከተገኙት ችግሮች 86 እስከ 92 በመቶ የሚሆኑት ላይ የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል።

በተጨማሪም ባለፉት 9 ወራት 3 ሺህ . በላይ የመስመር መልሶ ግንባታ የተከናወነ ሲሆን፣ 6 ከተሞች የኔትወርክ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው 10 ከተሞች ደግሞ በግንባታ ላይ ይገኛሉ።

በእነዚህ ሥራዎች በአዲስ አበባ የወርሃዊ የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽ እና የቆይታ ጊዜ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።

ሆኖም የመስመሮች ማርጀት፣ የፋይናንስ እጥረት፣ በዕቅድ የሚደረጉ ጥገናዎች መብዛት እና የመሠረተ-ልማት ስርቆት በዋና ተግዳሮትነት ተጠቅሰዋል።

ተቋሙ መጪውን የክረምት ወቅት ተከትሎ የተሻለ አቅርቦት ለመስጠት፣ በዕቅድ የሚሠሩ የፕሮጀክት ሥራዎችን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 . ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

ለአራተኛው ምዕራፍ የአዲስ አበባ መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ሲባል ለተፈጠረው መቆራረጥ ደንበኞቹን ይቅርታ የጠየቀው አገልግሎቱ፣ ማንኛውም የዕቅድ መቆራረጥ መርሐ-ግብር ከአንድ ቀን በፊት በማኅበራዊ እና በመደበኛ ሚዲያዎች እንደሚገለጽ አስታውቆ ኅብረተሰቡ መረጃዎችን እንዲከታተል ጥሪ አቅርቧል።

 

በአባዲ ወይናይ