በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቅምብቢት ወረዳ በበጋ መስኖ የለማው የስንዴ ሰብል ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን (ኮምባይነር) በመጠቀም የመሰብሰብ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም በወረዳው በመገኘት ይህንን የሰብል አሰባሰብ ንቅናቄ በአካል ተመልክተዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች ቀደም ሲል በነበረው ልማድ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ያመርቱ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን በበጋ መስኖ ልማት አማካኝነት በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ ማምረት መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይህ የሥራ ንቅናቄ የምርት መጠንን ከማሳደጉም በላይ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ እንዳጎናጸፋቸው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻልና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልልም ሁሉንም ወቅቶች በመጠቀም ለማምረት ሰፊ ስትራቴጂ መዘርጋቱን የጠቀሱት አቶ አወሉ፣ በተለይም በበጋ ወቅት ስንዴን ጨምሮ ሌሎች ጠቃሚ ሰብሎች እንዲመረቱ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም መሠረት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በበጋ ስንዴ አማካኝነት በዓመት ሁለትና ከዚያ በላይ ምርት እንዲገኝ እየተደረገ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
የአሁኑ የምርት አሰባሰብ ሂደትም ይበልጥ በቴክኖሎጂና በመካናይዜሽን የታገዘ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ያነሱት አቶ አወሉ፣ የክልሉ መንግሥት የአርሶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።