በየትኛውም መልክዓ ምድር ግዳጁን ሊወጣ የሚችል፣ በስልጠና እና በትጥቅ ዘመኑን የዋጀ ሠራዊት መንገባት ተችሏል ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጀኔራል ይመር መኮንን ገለጹ።
በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምስራቅ ዕዝ፣ ከወራት በፊት በቡርቃ ማሰልጠኛ ማዕከል በመሠረታዊ ውትድርና ተመርቀው ወደ ዕዙ ከተመደቡ በኋላ ከነባሩ ጦር ጋር የሚያዋሂድ ስልጠና ሲከታታሉ የቆዩ የሠራዊት አባላትን አስመርቋል።

በምረቃ መርሐ-ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጀኔራል ይመር መኮንን፥ የአስተሳሰብ ጥራት፣ ዕውቀት እና ስልትን መሠረት ያደረጉ ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎችን በመስጠት ሠራዊቱን በሥነልቦና እና በአቋም ብቁ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተና ጀኔራል አሰፋ ቸኮል፥ ሠራዊቱ ከሕዝቡ የተረከበውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የመጠበቅ አደራ ለማሳካት ከምን ጊዜውም ይልቅ በመትጋት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ኢትዮጵያ ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶች በተከታታይ የተቃጣበትን ጥቃት በድል የመከከተ መሆኑንም አውስተዋል።
በሰሜን ምስራቅ ዕዝ የቡርቃ ማሰልጠኛ ማዕከል ኃላፊ ኮሎኔል ግርማ ስዩም በበኩላቸው፥ የስልጠና ማዕከሉ ሠራዊቱ ተከታታይነትና ጥራት ያላቸው ስልጠናዎችን እንዲያገኝ የተሰጠውን ተልዕኮ በትጋት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በምረቃ መርሐ-ግብሩ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጀኔራል መኮንኖች እና ወታደራዊ አመራሮች እንዲሁም የአፋር እና የአማራ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በሁሴን መሐመድ