Search

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉዞ

ሰኞ ታኅሣሥ 20, 2018 480

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ማኅበረሰብን የሚያስከፉ ቁርሾዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ቁርሾዎች በመግባባት ካልተፈቱ በጊዜ ሂደት ከፍተኛ ቅራኔ እየፈጠሩ ሀገርን አደጋ ላይ ይጥላሉ፡፡ በሂደቱ የተጎዳው የማኅበረሰብ ከፍል የሚያነሳቸው ቅራኔዎች ሥር እየሰደዱ ወደ ግጭት እና ትጥቅ ትግልም ሊያመሩ ይችላሉ፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ሀገርን ወደ መበታተን ሊያደርሱ እንደሚችሉ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የረጅም ጊዜ የሀገረ መንግሥት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ የመጣችባቸው መንገዶች ውጣ ውረዶች የበዙባቸው ነበሩ፡፡ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ጉዞዋ በሚለዋወጡ ሥርዓቶች ውስጥ የተለያዩ የማኅበረሰብ ጥያቄዎች እየታፈኑ በሂደትም ወደ ትላልቅ ቅሬታዎች እያደጉ እዚህ ደርሰዋል፡፡ በተለይም ዘመናዊ ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያ በገባባቸው ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት የተፈጠሩ ሁኔታዎች የእነዚህ ቅራኔዎች ማሳያዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የሕዝብን ጥያቄ አንግበው ወደ ሥልጣን የሚመጡ ወገኖች የተነሱበትን የሕዝብ ጥያቄ እየዘነጉ አገዛዛቸውን ለማጽናት የሄዱባቸው መንገዶች ደግሞ ቀውሶቹን አባብሰው ሀገርን አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡

ታፍነው የቆዩ የሕዝብ ቅራኔዎች እየጋሙ መጥተው ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ኢትዮጵያን የመበታተን ጫፍ ላይ አድርሷት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጡ መንግሥትም ችግሮች በውይይት መፈታት እንዳለባቸው በማመን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከልም የብሔራዊ እርቀ ሰላም እና የማንነትና የወሰን ኮሚሽኖችን በማቋቋም ያደረጋቸው ሙከራዎች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ችግሮች ከመሰረቱ የሚፈቱት ሁሉንም ወገን ያማከለ ጥልቅ ውይይት ሲካሄድ መሆኑን ታምኖበትም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ ከሚሽኑ የሁሉንም ማኅበረሰብ ወኪሎች በማሳተፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ ቅራኔዎችን በአጀንዳነት በመያዝ ወደ መፍትሔ ሀሳብ የሚያመሩ ተግባራትን እያከናወነ ቆይቷል፡፡  

ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሁኔታ ከሀገር ወስጥ እና ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ በአካልም በመልዕክትም አጀንዳዎችን አሰባስቧል፡፡

ከግንቦት 2016 . ጀምሮ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ባካሄደው ምክክር እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተለያዩ የማኅበረሰብ ከፍልች ተሳትፈዋል፡፡

በየወረዳው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመምህራን ማኅበር፣ የሲቪል ማኅበራት፣ ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአሰሪዎች ማኅበራት፣ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣ የሙያ ማኅበራት፣ የክልል መንግሥታት አስፈጻሚ አካላት፣ የክልል ዳኞች፣ የክልል ምክር ቤቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሚዲያ ተቋማት (ጋዜጠኞች) ማኅበራት፣ የቀድሞ ሠራዊት ማኅበራት፣ የንግድ ማህበራት ምክር ቤት፣ የሴቶችና የወጣቶች ማኅበራት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የመንግስት ሰራተኞች እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በምክክሮቹ ተሳትፈዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ11 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን የመለየት እና አጀንዳ የማሰባሰብ ስኬታማ ሥራ ሠርቷል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግልጸኝነት እና አካታችነትን እውን ለማድረግም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋርም በበይነመረብም በአካልም አጀንዳ የማሰባሰብ እና ተወካዮችን የማስመረጥ ተግባራት አከናውኗል።

በትግራይ ክልልም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ምሁራን ጋር በሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥልቅ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ የትግራይ ክልልን ወክለው በዋናው ሀገራዊ ምክክር ላይ የሚሳተፉ አባላትን የተሳታፊዎች ልየታ፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራዎችን እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ታቅዷል፡፡

ከሚሽኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላትም በምክክሩ ተሳታፊ በመሆን አጀንዳቸውን እንዲያስይዙ ባደረገው ጥረት በርካቶች አጀንዳቸውን እንዲሰጡ አድርጓል፡፡

ቀጣይ ምዕራፍ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቀጣይ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እያከናወነ ነው፡፡

የኅብረተሰቡን ፍላጎት በማካተት በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማደራጀት እና ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ በትኩረት እየተሰራበት ነው፡፡

በዋና ዋና ሀገራዊ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማካሄድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመው እና ከ4 ሺህ በላይ ተወካዮች የሚሳተፉበት ዋናው ምክክር በመጪው ጥር መጨረሻ ይጀመራል።

ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ፣ መዋቅራዊ፣ የማንነት እና በማኅበረሰቡ የሚነሱ መሰረታዊ ችግሮች ላይ ተወያይቶ ትምህርት በመቅሰም  በሕዝቡ በራሱ መፍትሔ የሚገኝበት ነው።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሰበሰቡ አጀንዳዎችም ይህን የሚያመላክቱ ሲሆኑ፤ ሁሉም የተለዩ አጀንዳዎች እንደቅደም ተከተላቸው በዋናው ጉባኤ ይመከርባቸዋል፡፡

ከሚሽኑ ዋናውን ምክክር ሲያጠናቅቅም በሕዝቡ የሚሰጡ የመፍትሔ ምክረ ሀሳቦች ለመንግሥት እና ለአስፈፃሚ አካላት በማቅረብ፣ በሥራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፡፡

 

በለሚ ታደሰ