Search

"የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ አሳሳች በሆነ መልኩ የሚያስተጋቡ ታሪካዊ ጠላቶች ዓላማቸው ግልፅ ነው"፦ ዓለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር)

ሰኞ ታኅሣሥ 20, 2018 421

‎‎የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እየፈጠሩ ያሉት ትርክት፣ የኢትዮጵያን መልካም ስም የማጉደፍ ነው ሲሉ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስና የሕገ-መንግሥት መምህሩ አለማየሁ ገብረማርያም ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ፍትሃዊውን ጥያቄ የመስፋፋት ነው በማለት አሳሳች ፕሮፓጋንዳ እየሰሩ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።
‎የመደመር መንግሥት ከዚህ በፊትም በግልፅ እንዳስቀመጠው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትፈልገው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንደሆነ አስታውሰዋል።
‎ኤርትራ የሃገርነት ዕውቅና ባገኘችበት ወቅት፣ አሰብ በግዛቷ አለመካተቱን የሚያነሱት ሙሁሩ፤ በመሆኑም በሕግ አደባባይ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከራከር ይቻላል ባይ ናቸው።
‎አንድ ሃገር ነፃ ነኝ ብሎ ሲወጣ የያዘውን ግዛት ብቻ ይዞ እንደሚወጣ የሚያብራሩት ፕ/ር አለማየሁ፤ አሰብ በኤርትራ ስር እንዳልነበረ የሚታወቅ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ሕግ ይደግፈናል ብለዋል።
‎በቀጣናው ያለው ዋነኛ ችግር ድህነት ሆኖ ሳለ፣ በቀይ ባሕር ዙሪያ ያሉ ሃገራት ወደብን ጨምሮ ያላቸውን ሃብት ባለማልማታቸው ቀጣናው ለኢኮኖሚና ለፀጥታ ችግር ተጋልጦ ቆይቷል ይላሉ።
ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ እያደገ ካለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋር በትብብር ቢሰራ፣ በአጭር ጊዜ ለውጥ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
‎በቀይ ባሕር አካባቢ ከ10 ያላነሱ ከሩቅ የመጡ ኃያላን ሃገራት ባሕሩን እየተጠቀሙ፤ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያን የበይ ተመልካች የማድረግ ሴራ እዚህ ጋር ሊገታ ይገባል ብለዋል።
‎”ኢትዮጵያ በግልፅ እያለች ያለው በሰላማዊ መንገድ፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባሕር በር መውጫ ላግኝ ነው” ያሉት ዓለማየሁ ገብረማርያም (ፕ/ር) ለዚህ ደግሞ አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
‎የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እየሰሩት ያለውን የውሸት ትርክት ኢትዮጵያውያን የሃገሪቱን ትክክለኛ ጥያቄ በመረዳት መመከት እንዳለባቸውም ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
‎በሲሳይ ደበበ