Search

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባዎችን እንዲያከናውኑ ውክልና የሰጣቸው ተቋማት

ማክሰኞ ታኅሣሥ 21, 2018 401

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባዎችን የተለዩ የመንግሥት ተቋማት በውክልና አገልግሎቱን እንዲሰጡ ከስምምነት መድረሱን አስታውቋል።
አገልግሎቱ የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎትን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፤ ከሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ የሚገኘው መረጃ ሁሉንም መንግሥታዊ ተቋማትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በማንሳት፣ የምዝገባ ሥራውን በትብብር መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በዚህም አገልግሎቱ ከሚሰጠው የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት በተጨማሪ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለመከላከያ እና ለጤና ሚኒስቴር ውክልና መስጠቱን ጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወሰደው ውክልና መሰረትም እስከ ወረዳ በሚገኙ መዋቅሮች የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባውን በውክልና እንደሚያከናውን ተገልጿል።
ሌሎቹ እንደ መከላከያ እና ጤና ሚኒስቴር ያሉ ተቋማት የተመረጡ ወሳኝ ኩነቶችን የማሳወቅ ፈቃድ ያላቸው መሆኑም ተጠቅሷል።
ዋና ዳይሬክተሯ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ሥርዓት ዘመናዊ ማህበረሰብ በመፍጠር የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ጉልህ ለውጥ ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ መካከልም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ሶፍትዌር፣ በቀለለና በፈጠነ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት ለዲጂታል ማንነት መታወቂያ ሥርዓት ግንባታ፣ ለፖሊሲ ቀረፃ፣ ለሀገራዊ ልማት ዕቅዶች እና ለምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መሳካት የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ በአዲስ መልክ እንዲሻሻል ማድረጉን አንስተዋል።
ዲጂታል የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ የአስተዳደር፣ ፍትሕ እና የሀገር ደህንነትን በማረጋገጥ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
በሳምሶን በላይ