Search

አዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክም የዕውቅትም ቤት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ

ዓርብ ታኅሣሥ 24, 2018 58

ለ75 ዓመታት ለኢትዮጵያ የእውቀት ብርሃን ያበራው የዕውቀት ቤት - አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ!
በትጋት የሚመራ ምርምር፣ በሙግት የሚዳብር ሃልዮት፤ በአመክንዮ የሚበለጽግ ፍልስፍና የዩኒቨርሲቲው መለያ ቀለሞች ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የዕውቀት ብርሃን መፍለቂያ እና የለውጥ ጥሪ ማስተጋቢያ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ዛሬም የጀመርነውን ልማት በዕውቀት ለመምራት ተደማሪ ጉልበት ነው ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጽ አስፍረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከምሥረታው ጀምሮ የኢትዮጵያ የለውጥ እና የልማት ጥያቄዎች የፈለቁበት፤ የጊዜው ትንታግ ወጣቶች የለውጥ አብዮት የጎሰሙበት የታሪክም የዕውቅትም ቤት ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተደረገው ምክክርም ትናንት እና ዛሬን እንዲሁም ዛሬን እና ነገን፤ ዘላቂ ብልጽግናን ከተሳካ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጋር አሠናስሎ ለመምራት ጉልበት የሚሰጥ መሆኑን አመላክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ተምራችሁ፣ በዕውቀት ተኮትኩታችሁና ካባ ጭናችሁ ዛሬ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ተቋማት ለምታገለግሉ ምሁራንና ባለሙያዎች እንኳን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።
በተጨማሪም የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት በርትታችሁ እየተማራችሁ ላላችሁ ጥበብ ፈላጊ ተማሪዎች በሙሉ እንኳን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስትላልፈዋል።