የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲቃረብ የገና ባህላዊ ጨዋታዎችን መጫወት በኢትዮጵያ በተለይ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተለመደ ተግባር ነው፡፡
የገና ጨዋታ ከኃይማኖታዊ አንድምታዎቹ ባሻገር፣ ትውፊታዊ ገጽታዎች ያሉት ሀገር በቀል ባህላዊ የስፖርት ውድድር ነው፡፡
የገና ጨዋታ የዕድሜ ገደብ ሳይኖረው ከልጅ እስከ አዋቂ ያሉትን በማሳተፍ ከታህሳስ ጀምሮ እስከ ጥር ወር ይካሄዳል፡፡
የገና ጨዋታ የሚካሄደው ገና በመባል በሚጠራው ዱላ ከጫፉ ቀለስ ያለ ብዙ ጊዜ ከወይራ እንጨት በሚዘጋጅ እና የመጫወቻ ሩሯ (ጥንግ) ከቆዳ ጠፍር ወይም ከጉቶ ተጠርቦ ድቡልቡል ሆና በምትሰራው ነው፡፡
ጨዋታው በስፋት የሚካሄደው ሰብል በተሰበሰበበት አከባቢ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ በሁለት ቁጥራቸው እኩል በሆኑ ቡድኖች መካከል ሲሆን፣ ተጫዋቾች እግረ ጠባብ ልብስ እና ራሳቸው ላይ ሻሽ አስረው ይጫወታሉ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የገና ጨዋታውን የሚመራ አንድ ዳኛ ከአማካሪዎቹ ጋር በመሆን ከአራት የጎል ጠባቂዎች ጋር በጋራ ጨዋታውን ይመራል፡፡
ጨዋታው ሩሯን በገና ዱላው ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል በማንከባለል እና በመለጋት ነጥብ በማስቆጠር የሚካሄድ ነው፡፡
በገና ጨዋታ ብዙ አይነት ውድድሮች የሚከናወኑ ሲሆን ቁርቁዝ፣ ቀልቦ መለጋት፣ አፍሶ መለጋት እና ሙጭ የተሰኙ ውድድሮች ይደረጉበታል፡፡
የገና ጨዋታ የሁሉም መሆኑን ለመግለፅ እንዲሁም በጨዋታው ወቅት ለሚፈጠሩ ግጭቶች ቂም መያዝ እንደማይቻል ለማመላከት "በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ" እንዲሁም "በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ" እየተባለ ይዜማል፡፡
የገና ጫዋታ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ፌደሬሽን ጥናት አካሂዶበት ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ ሕግና ደንብ ተዘጋጅቶለታል፡፡
በዚህም በ2006 ተከልሶ በተዘጋጀው የባህልና ስፖርት ሰነድ መሠረት የገና ጨዋታ ወደ 7 የሚደርሱ ሕግና ደንቦች ተዘጋጂቶለታል፡፡
የገና መጫወቻ ሜዳ የጎል ጠባቂ፣ የተከላካይ፣ እንዲሁም የአጥቂ የማዕዘን መምቻ የሚሰመር ሲሆን የሜዳ ስፋቱ ደግሞ ርዝመቱ 90 ሜትር ጎኑ 50 ሜትር ሆኖ ይዘጋጃል፡፡
ሜዳ ውስጥ ለመጫወት ሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች 15 ተጫዋቾችን ያቀርባሉ፡፡ 10ሩ ሜዳ ውስጥ ገብተው ሲጫወቱ 5ቱ ደግሞ በተቀያሪ ወንበር ይቀመጣሉ፡፡
ጨዋታውን የሚመራ የማሕል ዳኛ፣ ዳኛውን የሚያግዙ የመስመር ዳኞች እና ተቀያሪ ተጫዋቾችን የሚቀይሩ ዳኞችም ይኖራሉ፡፡
አንድ የገና ጨዋታን ለማካሄድ በሁለት የ30 ደቂቃ አጋማሾች የተከፈለ እና የ10 ደቂቃ እረፍት ያለው 60 ደቂቃ ያስፈልጋል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ተጨማሪ 15 ደቂቃ ይሰጣል፡፡ በዚህም ካልተሸናነፉ የቅጣት ምት እየተሰጠ አሸናፊው ይለያል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ