ኢትዮጵያ በታሪኳ ጠንካራ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
ይህ የታሪክ አሻራ በተለይም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) መቀመጫውን አዲስ አበባ እንዲያደርግ በማስቻል ረገድ የላቀ ሚና ተጫውቷል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ጉባኤ ማስተናገድ የቻለችው በታሪካዊ ነጻነቷ እና በነበራት የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ነው።
እ.ኤ.አ. በ1958 የተመሰረተው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫውን አዲስ አበባ እንዲያደርግ የተወሰነው በወቅቱ በነበረው ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነው።
በወቅቱ የሥራና መገናኛ ሚኒስትር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እንደሚገልጹት፤ የኮሚሽኑ መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ ለመዲናዋ ዘመናዊ የከተሜነት ታሪክ እና ለግዙፍ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ዋነኛ መነሻ ሆኗል።
የአፍሪካ አዳራሽ (Africa Hall) ከመገንባቱ በፊት ስብሰባዎች የሚካሄዱት በወቅቱ በነበሩት የመከላከያ ሚኒስቴር እና የንግድ ሥራ ኮሌጅ አዳራሾች ውስጥ ነበር።
ይሁን እንጂ አህጉራዊ ውይይቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለማካሄድ ዘመናዊ አዳራሽ መገንባት የግድ አስፈላጊ በመሆኑ የአሁኑ የአፍሪካ አዳራሽ ግንባታ ተጀመረ።
ይህ ፍላጎትም ለቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እና ከመሃል ከተማ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ለሚወስደው ዘመናዊ መንገድ መሰራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው።
ለህንጻው ግንባታ በወቅቱ አምስት ሚሊዮን ብር እና ሦስት ዓመታት ጊዜ እንደሚፈጅ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፤ ግንባታው በአንድ ዓመት ውስጥ መጠናቀቅ እንዳለበት በመወሰኑ "ባርኔሮ" የተባለ የውጭ ተቋራጭ ሥራውን ተረክቦታል።
በሦስት ዓመት የሚጠናቀቀውን ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ለማጠናቀቅ ሰራተኞች ለ24 ሰዓታት ያለምንም ማቋረጥ እንዲሰሩ ተደርጓል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለፕሮጀክቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ በእኩለ ሌሊት ሳይቀር በቦታው ተገኝተው የሥራውን ሂደት ይከታተሉ ነበር።
ይህ ጥረት ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ. በ1963 የአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) መመስረቻ ቻርተርን በዚሁ ታሪካዊ አዳራሽ ውስጥ ለመፈረም በቅተዋል።

ዛሬም ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ሚናዋን በማስቀጠል በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በብቃት ማስተናገዷን ቀጥላለች።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ