በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቀድሞ ምክትል ኃላፊን ጨምሮ 11 አመራሮችና ሰራተኞች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ168 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ጉዳት አድርሰዋል በሚል ተጠርጥረው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።
የምርመራ መዝገቡ እንደሚያመለክተው፤ ተጠርጣሪዎቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 "አየር መንገድ" አካባቢ የሚገኝንና ለሕዝብ መናፈሻነት የተከለለ ሥፍራ በጥቅም በመመሳጠር ለግል ማህበር አሳልፈው ሰጥተዋል።
በ2016 ዓ.ም በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው አየር መንገድ አከባቢ የህዝብ እና የመንግሥት ይዞታ የሆነውን በ9ኛው መዋቅራዊ ፕላን በዓድዋ ፓርክነት ተይዞ የነበረውን እና በ10ኛው ደግሞ ለ"ዊንዶው ኦፍ አፍሪካ" ፕሮጀክት በመናፈሻነት የተያዘና በመሬት ባንክ ውስጥ ያለ ይዞታ መሆኑ ተገልጿል።
ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ ያለ ሕጋዊ ምክንያት "ሰነድ አልባ ይዞታ ነው" በሚል 2 ሺህ 905 ካሬ ሜትር ቦታ ለዮርዳኖስ፣ ዘውዲቱ እና ጓደኞቻቸው የሲሚንቶ አከፋፋይ ህብረት ሽርክና ማህበር እንዲተላለፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።
በዚህም መንግሥት ማግኘት የነበረበትን 168 ሚሊዮን 724 ሺህ 405 ብር የሊዝ ዋጋ እንዲያጣ በማድረግ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብሏል።
በሙስናው ወንጀል የተጠረጠሩት እና በቁጥጥር ስር የዋሉት አመራሮችና ባለሙያዎች ስም ዝርዝር ቀጥሎ ቀርቧል፦
1. አቶ ሞሊቶ አባይነህ ኤርቃሎ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ የቀድሞ ም/ኃላፊ
2. ኢ/ር ቸርነት አበበ ያደቴ፦ የቦሌ ክ/ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት የቀድሞ ኃላፊ
3. ሰለሞን በላይ መኮንን፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ የቴክኒክ ጉዳይ ወሳኝ ባለሙያ
4. አድማሱ አዳነ ወንድሙ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ የቅሬታ እና አቤቱታ ባለሙያ
5. ግዛቸው ሙሉጌታ ደሴ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ ይዞታ ማስተካከል ቡድን መሪ
6. ደረጀ ጎሹ ሀይሌ፡-የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ
7. አለምፀሃይ ለማ ኪ/ማርያም፡- የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 መሬት ልማትና አስተዳደር የሰነድ አጣሪ ባለሙያ
8. ግርማ ተፈራ አያና፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳዳር ቢሮ ህግ/ቴክኒክ ጉዳይ ክትትል ዳይሬክተር
9. አማኑኤል አለማየሁ ማሞ፡- የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 የቴክኒክ ባለሙያ
10. ቢኒያም ሀይሉ ገብሬ፡- የቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 13 የቴክኒክ ባለሙያ
11. አቢዮት ጁፋሬ ባይሳ፡- በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ
የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበሩ በቁጥጥር ስር ውለው በፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የጀመረውን የምርመራ ሂደት ለማጠናቀቅ ከፍርድ ቤት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ምርመራውን እያካሄደ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።