አፍሪካ የራሷን አጀንዳ የመቅረጽ እና የማስተዳደር ሙሉ አቅም ላይ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ አህጉሪቱ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ጠቁመው፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለጋራ ዕድገትና ለቀጣናዊ ትስስር የመጠቀም አስፈላጊነት ላይ ትኩረት አድርገዋል።
ውኃን እንደ ተራ ሀብት ብቻ ሳይሆን እንደ ልማት መሣሪያ፣ የፈጠራ መነሻ እና ለቀጣናዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን አብራርተዋል። ይህም ለከተሞች ዕድገት፣ ለግብርና፣ ለጤና እና ለጠቅላላ ሰላም ወሳኝ ቁልፍ መሆኑን አስምረውበታል።
ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን በጥንቃቄ ለልማት ማፋጠኛ እየተጠቀመች መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እንደ አብነት አንስተዋል።
ግድቡ በአሁኑ ወቅት ለመኖሪያ ቤቶችና ለኢንዱስትሪዎች ኃይል ማቅረብ መጀመሩን ገልጸው፣ ለጎረቤት ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል በማጋራት ቀጣናዊ ትስስርን እያጠናከረ ይገኛል ብለዋል።
ይህ ስኬት አፍሪካውያን የጋራ ሀብታቸውን በፍትሃዊነት ተካፍለው ለጋራ ዕድገት እንዴት መሥራት እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአፍሪካ መንግሥታት ለጋራ ብልጽግና በቁርጠኝነት የሚሠሩ ከሆነ፣ አህጉራዊ ወንዞች የክርክር ምንጭ መሆናቸው ቀርቶ ለዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ዋነኛ መሣሪያ እንደሚሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አሳስበዋል።
በለሚ ታደሰ