የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ምዝገባ የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) አስገዳጅ የሚሆነው ዜጎች በዲጂታል አማራጮች በሚመዘግቡበት ወቅት ብቻ መሆኑን አስታወቀ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በሰጡት ማብራሪያ፤ የብሔራዊ መታወቂያ ለምዝገባ አስፈላጊ የሚሆንበትን ምክንያት እና ያሉትን አማራጮች በዝርዝር ገልጸዋል።
እንደ ሰብሳቢዋ ገለጻ፣ አንድ ሰው በራሱ ስልክ "ምርጫዬ" መተግበሪያን በመጠቀም ለመመዝገብ ሲፈልግ ማንነቱን ለማረጋገጥ የፋይዳ ባዮሜትሪክስ መረጃዎች (ፎቶግራፍ እና አሻራ) ወሳኝ ናቸው።
ይህ አሠራር በዋናው የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1162 ላይ የተደረገው ማሻሻያ አካል መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ፣ ራስን በራስ የመመዝገብ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ በዲጂታል አገልግሎት ፋይዳን መጠቀም የግድ እንደሚል አስረድተዋል።
በሌላ በኩል፣ በመደበኛው አሠራር ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመሄድ ለሚከናወን የምዝገባ ሂደት የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) መኖር ግዴታ አለመሆኑን ቦርዱ አረጋግጧል።
በአካል ለሚመዘገቡ ዜጎች በብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) መመዝገብ የሚችሉ ሲሆን፤ የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) የሌላቸው ዜጎች ደግሞ በመደበኛው የነዋሪነት መታወቂያ መመዝገብ ይችላሉ።
ከዚህም ባለፈ የነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸው ወይም ማቅረብ የማይችሉ ዜጎች በምስክር አማካኝነት ማንነታቸውና ነዋሪነታቸው ተረጋግጦ መመዝገብ የሚችሉበት አሠራር ተመቻችቷል።
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አስፈጻሚዎች የብሔራዊ መታወቂያን እንደ ብቸኛ አማራጭ አድርገው በመጠየቅ ምዝገባ ላይ መጉላላት እንደሚፈጥሩ የገለጹት ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ይህ ችግር የሚመነጨው ከግንዛቤ እጥረት መሆኑን ጠቁመዋል።
ቦርዱ ችግሩን ለመቅረፍ ለአስፈጻሚዎች ግልጽ መመሪያ በመስጠት በየጊዜው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየሠራ መሆኑንና በቀጣይም በአካል ለሚደረግ ምዝገባ ብሔራዊ መታወቂያ አስገዳጅ አለመሆኑን የማሳወቅ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ