ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ዕጩዎችን እና መራጮችን የመመዝገብ፣ የፓርቲዎችን በጀት የማስተዳደር እና የምርጫ ክርክሮችን የማመቻቸት ሥራዎች በስኬት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በመላ ኢትዮጵያ የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ ለ169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ ምርጫውን ለመታዘብ ደግሞ 55 ድርጅቶች ተመዝግበዋል።
እስካሁን በብሔራዊ ደረጃ 7 የምርጫ ክርክሮች የተካሄዱ ሲሆን፣ በቀጣይ በክልል መገናኛ ብዙኃን ጭምር የሚተላለፉ ክርክሮች እንደሚቀጥሉ ታውቋል።
ለዚህም ለፖለቲካ ፓርቲዎች የነፃ የአየር ሰዓት ድልድል ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል ሰብሳቢዋ።
ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተ እስካሁን 81 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል።
ምርጫውን ለመዘገብም ወደ 37 መገናኛ ብዙኃን ፈቃድ መውሰዳቸውንም ነው ሰብሳቢዋ የጠቀሱት።
የዕጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በትክክል መከናወናቸው ተገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ቀጣይ የሥራ ምዕራፎችን ውጤታማ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሰብሳቢዋ አረጋግጠዋል።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #generalelections #Observers #VoterEducation #CSOs #PoliticalParties #NEBE #EBC