ባለፉት ዓመታት በትግራይ ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የአመለካከትና የንቃት ለውጥ እየታየ መሆኑን የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ገለጹ።
ወጣቱ አሁን ላይ የፖለቲካ ሴራዎችን በመረዳት "ለጥቂት ግለሰቦች ስልጣን ሲባል አልሞትም" የሚል ጠንካራ አቋም እየያዘ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
ወይዘሮ ኬሪያ ከኢቢሲ የ"ስለ ሀገር" ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳluት፣ በትግራይ የሚገኘው ወጣት ካለፈው የጦርነት መከራ በመማር አሁን ያለውን የጦርነት ነጋሪት በንቃት እየተቃወመ ይገኛል።
ወጣቱ ቀደም ሲል "ለህዝብ ሕልውና" ተብሎ ይነገረው የነበረው ትርክት፣ አሁን ላይ "የጥቂት መሪዎችን ስልጣን ለማስጠበቅ" የሚደረግ ድራማ መሆኑን በውል ተረድቷል ብለዋል።
"የእነርሱን ሕልውና ለማረጋገጥ መሞት እንደሌለበት ወጣቱ አሁን ገብቶታል" ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፣ ይህ ግንዛቤ በሕወሃት ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩን ገልጸዋል።
የትግራይ ወጣቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች በግልጽ ቋንቋ እየዘፈኑ "ጦርነት ይበቃናል፤ ሰላም እንፈልጋለን" እያሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ወጣቶች ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውንና የሰላም ናፍቆታቸውን መግለጻቸው፣ በብሔር የመሸሸግ የቆየ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች የማይመች መሆኑን አስረድተዋል።
በትግራይ እናቶችና ወጣቶች ዘንድ አሁን ትልቅ ሐዘንና ቁጭት መኖሩን የገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ፣ አንዲት ወጣት በትግርኛ የተናገረችውን ዋቢ በማድረግ አስረድተዋል።
"ለእናቴ ጀግና ሆኜ መሞት ሳይሆን፣ ጀግና ሆኜ መኖርና እናቴን መርዳት እፈልጋለሁ" የሚለው የወጣቷ ንግግር የብዙኃኑ ወጣት ጽኑ አቋም መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ሐቅን መቀበልና በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ መሪዎቹን መሞገት መጀመሩ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ለውጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የወጣቱ የአመለካከት ለውጥ በትግራይ ያለውን የኃይል ሚዛን እንደሚያስተካክለውና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ
#Ethiopia #Tigray #YouthAwakening #Peace #KeriaIbrahim #SileHager #EBC