ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሰበር ዜና በሚል የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ተንቀሳቃሽ ምስል ሲዘዋወር እና የበርካቶችም መነጋገሪያ አጀንዳ ሲሆን ተስተውሏል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ "ጄሲካ ራድክሊፍ" የተባለች የባህር እንስሳት አሰልጣኝ (አልማጅ) "ኦርካ" ከተባለ ዶልፊን መሰል ዓሳ ነባሪ ጋር እየዋኘች አዝናኝ ትርኢት በማቅረብ ላይ ሳለች በእንስሳው ተበልታ ሕይወቷ እንዳለፈ የሚያሳይ አስደንጋጭ ምስል ነው።
ታዲያ ይህ ተንቀሳቃሽ ምስል በቲክቶክ፣ በዩቲዩብ እና በፌስቡክ በሰበር ዜና መልክ ተሰራጭቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተመለከቱት እና መነጋገሪያ ያደረጉትም ለመሆን ችሏል።
አስገራሚው ጉዳይ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተሰራ እና ሐሰተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በግዙፉ የባሕር ዓሳ ተበልታ ሕይወቷ አልፏል የተባለችው የ23 ዓመት ወጣት "ጄሲካ ራድክሊፍ" የልብ ወለድ ፈጠራ ገጸ-ባሕርይ መሆኗም ጭምር ነው።
ከሰለጠነ ኦርካ፣ ዶልፊን፣ ሲላ እና መሰል የባሕር እንስሳ ጋር አዝናኝ ትዕይንት ማቅረብ በምዕራባውያን ሀገራት የተለመደ እና በርካቶችም በመዝናኛ ስፍራዎች ተገኝተው የሚከታተሉት ነው።
ይህን አዝናኝ ትዕይንት የሚያሳዩ በርካታ እውነተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ይገኛሉ።
ይህን በማስመሰል የልብ ወለድ ፈጠራ ታሪክ እና ተዋናይ ተመርጦለት እንደቀልድ በኤአይ ተሰርቶ የተጫነውና ኦርካው አደጋ ሲያደርስ የሚያሳየው ቪድዮ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ሲሰራጭ የበርካቶችን ቀልብ ሊገዛ ችሏል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየው ስፍራ የሚቀያየር መሆኑ፣ አንድ ጊዜ በቤት ውስጥ ያለ አንድ ጊዜ ደግሞ ጣሪያው ክፍት በሆነ ስፍራ ላይ መታየቱ ምስሉ በኤአይ የተሰራ እንደሆነ ያመለክታል።
ሌላው ከእንስሳው ጋር ትዕይንት የምታሳየው እንስት ተክለ ሰውነትም እንደዚሁ ከተፈጥሮ በወጣ መልኩ የሚቀያየር መሆኑ እና የተለያዩ ግለሰቦችን እንደ አንድ ሰው አስመስሎ ማቅረቡ በቀላሉ ምስሉ በኤአይ የተሰራ መሆኑን ለማረጋገጥ ያስችላል።
"ዘ ስታር" የተሰኘው ዓለም አቀፍ ሚድያም ሙሉ ተንቀሳቃሽ ምስሉ በኤአይ የተሰራ ሐሰተኛ ስለመሆኑ እና "ጄሲካ ራድክሊፍ" የልብ ወለድ ፈጠራ ገጸ-ባሕርይ ስለመሆኗ ማረጋገጡን ዘግቧል። በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚሰማው ድምፅም እንደዚሁ በኤአይ የተሰራ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል "ዘ ስታር" በዘገባው።
#ebcdotstream #etv #EBC #FactCheck #fakenews #Scams #cybersecurity