ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚድያዎች እና በሙዚቃ ማሰራጫ ፕላትፎርሞች ላይ በታዋቂ ድምፃዊያን ስም አዳዲስ ነጠላ ሙዚቃዎች እና የሙዚቃ አልበሞች እንደወጡ ተደርጎ እየተለቀቁ በርካቶችንም እያታለሉ እንደሚገኝ ይገለፃል።
ያለ ሙዚቀኞቹ እውቅና ተሰርተው በታዋቂ ሙዚቀኞች ስም የሚለቀቁት እነዚህ አዳዲስ ሙዚቃዎች ታዲያ ሙሉ ለሙሉ በኤአይ (AI) የሚሰሩ እና በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚለቀቁ ናቸው።
ታዲያ ከሰሞኑ ከወደ እንግሊዝ የተሰማው ተመሳሳይ ታሪክ ነው፤ በታዋቂዋ ድምፃዊት በኤሚሊ ፖርትማን ስም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ተሰርተ የወጡ ሁለት አልበሞች በርካታ ሰዎች ጋር ደርሰው ተወዳጅነትንም ማትረፍ ይጀምራሉ።

ኤሚሊ ፖርትማን ስም የተለቀቀውን “ኦርካ" የተሰኘ አዲሱን አልበም በማሞገስ የአድናቆት መልእክቶች ለአርቲስቷ ይጎርፉላት ጀመር፤ በነገሩ ግራ የተጋባችው ድምፃዊት የተላከላትን ሊንክ ተከትላ ሙዚቃውን ስትሰማ ማመን እንዳልቻለች ትናገራለች።
ምክንያቱም ታዋቂዋ ዘፋኝ ምንም አዲስ አይነት አዲስ ዘፈን አላወጣችም። ነገር ግን በሷ ስም በስፖትፋይ ፣ አይትዩንስ እና ሌሎች የሙዚቃ ማሰራጫ መድረኮች ፣ ሁሉ ዘፈኖቹ ተለቅቀዋል።
ምን እንደሆነ የማወቅ ጉጉት ያደረባት ዘፋግኟ ፣ የዘፈኑን ሊንክ ከፍታ ስትመለከት የሰማችው ሙዚቃ፣ የዘፈን አርእስቶች እና የራሷን የሚምሰል ድምጽ ጭምር በተመለከተች ሰዓት ነገሩ “አስፈሪ እንደነበር ተናገራለች።
ከዚህ በላይ ነገሩን ከባድ ያደረገው ደግሞ አንዳንድ አድማጮች የእሷ ዘፈን ስለመሆኑ እርግጠኞች ነበሩ።
ከቀናት በኋላ ነገሩ እየተባባሰ ሄዶ ሁለተኛ አልበም በገጿ ላይ በድጋሚ ታየ ፣ በዚህ ጊዜ አልበሙ 20 ትራኮች ነበሩት።

በስተመጨረሻ ፖርትማን ሁለቱም የውሸት ዘፈኖች እንዲወገዱ በፍጥነት የቅጂ መብት ቅሬታዎችን አቅርባለች።
ያም ሆኖ ሁሉም ሰው እውነቱን አልተረዳም። ይህም ሰዎች እንዴት በቀላሉ ሊታለሉ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
በአገራችንም በዩቲዩብ ላይ በተመሳሳይ መልኩ በታዋቂ አርቲስቶች ስም በአማርኛ ቋንቋ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰሩ ነጠላ ሙዚቃ እንደወጣ ተደርጎ አንዳንድ ጊዜ ከክሊፕ ጋርም ጭምር የሚጫኑ እና በሺዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቻቸው ጋር የሚደርሱ ሀሰተኛ የሙዚቃ ስራዎች ይስተዋላሉ።
ታዲያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰሩ ሙዚቃዎችን ለመለየት ምን ማድረግ ይቻላል? ምን አይነት ጥንቃቄስ ማድረግ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች እንደሚሆን ይገመታል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በተሰሩ ሙዚቃዎች ላለመሸወድ፦
1. ትክክለኛ የአርቲስቶቹን የማህበራዊ ትስስር ገፆች በመለየት መከታተል
2. የሚታየው የሙዚቃ ክሊፕ አልያም ሙዚቃ በአትኩሮት መመልከት፤ በበሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰሩ ሙዚቃዎች ብዙውን ጊዜ ትርጉም የማይሰጡ ግጥሞች እና የተበታተነ እና ወጥነት የሌለው ታሪክ ይኖራቸዋል
3. የምስሎች መደጋገም፣ የቃላት እና የዜማ መደጋገምም ሌላኛው መለያ መንገድ ሊሆን ይችላል።