*********
ከ2.5 ቢሊዮን በላይ የጂ-ሜይል አካውንቶች ለጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን የጉግል ኩባንያ ይፋ አድርጓል።
ከሰሞኑ ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉግል የጂ-ሜይል ተጠቃሚዎች ለጥቃት መጋለጣቸውን ተከትሎ ተጠቃሚዎች የይለፍ ቃሎቻቸውን እንዲቀይሩ አሳስቧል።
ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን የጂ-ሜይል ማስጠንቀቂያን የመረጃ መንታፊዎች እንደ መረጃ ማጥመጃ ስልት አድርገው እየተጠቀሙ መሆኑን ተከትሎ አብዛኛዎቹ የጂ-ሜይል ተጠቃሚዎች የጥቃት ሰለባ መሆናቸው ነው የታወቀው።
ጉግል ኩባንያ የጂ-ሜይል አካዉንቶችን ደህንነት ከመረጃ ጠላፊዎች የሚጠብቅበት አንዱ መንገድ የአካውንት የደህንነት እንቅስቃሴ ማስጠንቀቂያዎችን ለተጠቃሚዎች በማድረስ እና በማረጋገጥ መሆኑ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ይህን የጉግል ጂ-ሜይል የማስጠንቀቂያ መንገድ የመረጃ ጠላፊዎች የሳይበር ጥቃት ማድረሻ አማራጭ አድርገው እየተጠቀሙበት መሆኑ ተጠቁሟል።
በመሆኑም ከማስጠንቀቂያ ጋር የሚመጡ የጂ-ሜይል ማስፈንጠሪያዎችን አለመተግበር ብሎም የአካውንት ደህንነት ወይም ሴኩሪቲ ሴቲንግ ውስጥ በመግባት ከእርስዎ እንቅስቃሴ ውጭ የሆኑ ክስተቶች እና ዲቫይሶች ካሉ ወዲያውኑ የይለፍ ቃል መቀየር ዋነኛ መፍትሔዎች እንደሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህም ባሻገር እንደ ፓስኪ፣ ባለብዙ ማረጋገጫ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የተለያዩ የጂ-ሜይል አካውንቶችን መጠቀም ተጨማሪ መፍትሔዎች መሆኑን ፎርብስን ጠቅሶ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስነብቧል።