አሰብ ሲነሳ ለብዙዎች የካርታ ላይ መስመር ወይም የፖለቲካ መነጋገሪያ ሊሆን ይችላል፤ ለእኔ ግን የደም ስሬ፣ የልጅነት ትውስታዬና የአባቴ የዕድሜ ልክ ናፍቆት ነው።
አባቴ ፈንታው አደም በአሰብ ነጋዴ ሰፈር ስሙ ገዝፎ የሚነሳ፣ በንግዱና በሥራ ወዳድነቱ የሚታወቅ ብርቱ ሰው ነበር። አሰብ ለእሱ መኖሪያ ብቻ ሳትሆን ማንነቱ፣ ሀብቱና ክብሩም ነበረች።
የ1983 ዓ.ም የመለያየት ንፋስ ሲነፍስ ወንድሞቼና እህቶቼ በጅቡቲ በኩል ተሰደዱ፤ አባቴ ግን "ሀገሬን ጥዬ አልወጣም" ብሎ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ከአሰብ ጋር ግብግብ ገጠመ። በ1986 ወይም 87 አካባቢ አሰብን ለቆ የወጣው የመጨረሻው ተፈናቃይ እሱ ነበር።
ከአሰብ ቢወጣም ልቡ ግን እዛው ቀርቷል። ኮምቦልቻ ካምፕ ውስጥ ተጠልሎ ሳለ እንኳ በረሃውና የለመደው የንግድ ግርግር እየመጣ ሲቀሰቅሰው "የአሰብ ተፈናቃይ" የሚለውን ስም ሊለምደው አልቻለም። ናፍቆቱ ሲበዛበት ለአሰብ ቅርብ ወደሆነችው ዲቺኦቶ (በአፋር ክልል በአሁኑ የኤሊዳር ወረዳ ውስጥ የምትገኘ የንግድ ቦታ ነች) ተመልሶ መነገድ ጀመረ፤ ሁሌም ግን ከጓደኞቹ ጋር ቁጭታቸው አንድ ነበር "አሰብ ተመልሰን ሄደን የድሮ ሕይወታችንን በኖርን" የሚል፡፡
አባቴ በ2007 ዓ.ም አላህ ይርሃመውና ከዚህ ዓለም ሲለይ፣ ያንን ትልቅ ተስፋና ቁጭት በእኔ እጅ አስቀምጦ አልፏል። ዛሬ እኔ ጋር የአባቴ ንብረት የሆኑ የቤትና የንግድ ቦታዎች ሕጋዊ ካርታዎችና ሰነዶች አሉ። "ይሄ የእኛ ነው" እያለ ያሳየን የነበረው ያ የንግድ ቦታና የመኖሪያ ቤት ዛሬም በዓይነ ሕሊናዬ ይርመሰመሳል።
አሁን የወደብና የአሰብ ጉዳይ ሲነሳ "የአባቴ ምኞት በእኔ ዘመን እውን ይሆን ይሆን?" የሚለው ጥያቄ በውስጤ በኃይል ይጮኻል።
አሰብ ለኮምቦልቻ፣ ለባቲና ለአካባቢው ሕዝብ የሕልውና መሠረት፣ የንግድ መፍለቂያና የትልቅ ተስፋ ምድር ነበረች። እኔ የአባቴን ታሪክ የምሸከም፣ ሰነዱን የያዝኩ ሕጋዊ ወራሹ ነኝ።
ያ የቁጭት ታሪክ ተቀይሮ፣ አባቴ በሕይወት እያለ ያላየውን ያንን የወደብ ብርሃን እኔ ሄጄ የማየውና ለእናንተም በደስታ የምነግራችሁ ቀን ቅርብ እንደሆነ አምናለሁ። የታሪክ ፍትህ የአባቴንና የሺዎችን ቁጭት የሚያብስበት ጊዜ ይመጣል።
የኢቢሲዋ ጋዜጠኛ ሃያት ፈንታው እንደተረከችው
#Ethiopia #Assab #History #Identity #ኢትዮጵያ #አሰብ #የወደብጉዳይ #ቁጭት #ትውስታ