የሀገርን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚቻለው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በአንድነት እና በኃላፊነት ስሜት ሲቆሙ መሆኑን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን 36 ጋዜጠኞች በምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሀገር እንዳትዳከም ማድረግ የሚቻለው በጋራ በመቆም መሆኑን ጠቁመው፣ ባለሙያዎች በማንኛውም ዘገባዎቻቸው ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባሻገር የሀገርን ኅልውና በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተር ጄኔራሉ፣ ጋዜጠኞች በዚህ ረገድ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ለመኖር፣ ለመዝለቅ እና ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም በማስገንዘብ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የተረዳ የሚዲያ ባለሙያን ማፍራት ደግሞ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጥቅም ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል የተሻለ መደላድልን ይፈጥራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፣ በሙያ ሥነ-ምግባር እና በልኅቀት የታነፀ ጋዜጠኛ ለሀገር ግንባታ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል።
ለ21 ቀናት በባለሥልጣኑ የልኅቀት ማዕከል ሲሰጥ የቆየው ይህ የልዩ ትኩረት ዘርፍ ጋዜጠኝነት ሥልጠና፣ በዘርፉ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና መገናኛ ብዙኃኑን የሚያዘምን መሆኑን ተናግረዋል።
ሠልጣኞቹ በቆይታቸው በሀገራዊ ጥቅም፣ በሙያዊ ሥነ-ምግባር እንዲሁም በፖሊሲ እና ስትራቴጂዎች ዙሪያ ጥልቅ ግንዛቤ ማግኘታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ይህ የልኅቀት ጉዞ መጀመሪያ እንጂ መዳረሻ ባለመሆኑ ባለሙያዎቹ በየተቋሞቻቸው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡና ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮችን ለሕዝብ በበቂ ሁኔታ እንዲያሳውቁ አሳስበዋል።
በብሩክታዊት ተገኝ