Search

ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ፦ የየብስ ተከልነት ፈተናዎች፣ የጂኦፖለቲካ ትኩሳት እና የትውልድ ተልዕኮ

ቅዳሜ መጋቢት 12, 2018 138

ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ተራ የውኃ አካል ወይም በካርታ ላይ የሚታይ ሰማያዊ ቀለም ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የኅልውናዋ መሠረት፣ የታሪኳ መገኛ እና የኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት ነው።

ኢትዮጵያ ከጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በባሕር በር ባለቤትነቷ የምትታወቅ የባሕር ኃይል ሀገር ነበረች።

ሆኖም፣ የታሪክ አጋጣሚዎች፣ የቅኝ ግዛት ሴራዎች እና የውስጥ የፖለቲካ ስህተቶች ሀገራችንን ዛሬ ላለችበት የየብስ ተከል ሀገር’ (Landlocked) ሁኔታ ዳርገዋታል።

ታሪካዊ ዳራ፦ ኢትዮጵያ እና የባሕር በር ትግል

የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ግንኙነት የሺህ ዓመታት ዕድሜ ያለው ነው። ጥንታዊው የአክሱም ሥልጣኔ በዓለም ላይ ከነበሩት ታላላቅ መንግሥታት አንዱ ለመሆን የቻለው በቀይ ባሕር ላይ በነበረው የበላይነት እና በአዱሊስ ወደብ አማካኝነት በፈጠረው የንግድ ትሥሥር ነው።

በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ መሪዎች የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር እና የባሕር በሯን ለማስመለስ ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል።

እነዚህ የኢትዮጵያ ወሰኖች በሕዝብ አጥንት የተገነቡ እና በደሙ የተለሰኑ የትውልድ አደራ ያለባቸው መሬቶች በመሆናቸው፣ ይህንን ድንበር መደፈር ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ የሚያቆስል ጉዳይ ነው።

የዘመናት ሴራ፦ ኢትዮጵያን ከባሕር የማራቅ ታሪካዊ ፈተና

የኢትዮጵያ እና የቀይ ባሕር ግንኙነት ሲነሣ፣ ሀገራችንን ከባሕር ዳርቻዋ ለመነጠል የውጭ ጠላቶች ያደረጉት ተከታታይ ሴራ አብሮ ይነሣል። የኢትዮጵያ ባዕዳን ጠላቶች በየዘመኑ የተለያዩ ስልቶችን ሲጠቀሙና ታሪካዊ ሴራዎችን ሲፈጽሙ ኖረዋል።

የእነዚህ ኃይሎች ዋነኛ ስትራቴጂ ኢትዮጵያን በየብስ ቁልፍ ውስጥ በማስገባት ማነቅ እና ማዳከም ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያ ዝም ብላ እጇን አልሰጠችም። የጥንቱን ታሪክ እናቆየውና፣ የቅርብ ዘመናት የኢትዮጵያ መሪዎች የኢትዮጵያን የባሕር በሮች ለማስመለስ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል።

እነዚህ የኢትዮጵያ ነገሥታት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ያደረጉት ተጋድሎ፣ ወሰኖቹ በኢትዮጵያ ሕዝብ አጥንት የተገነቡ እና በደሙ የተለሰኑ ክቡር መሬቶች መሆናቸውን ያስመሰክራል።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም ቢሆን፣ የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋሐድ በኃያላን መንግሥታት ዳኝነት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ለብዙ ዓመታት ፋታ የሌለው ሙግት አድርጓል።

ይህ የትውልዶች ቅብብሎሽ ያሳየው፣ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ርቃ መኖር እንደማትችል እና መብቷን ለማስከበር ሁሌም እንደምትታገል ነው። በዚህም ጥረት ኤርትራ በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል እና ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን ተወስኖ ነበር።

የሕግ እና የተፈጥሮ መብት (አሰብ የማናት?)

ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም “አሰብ የማናት?” በተሰኘው መጽሐፋቸው አሰብ የኢትዮጵያ ሕጋዊ እና ተፈጥሯዊ የባሕር በር መሆኗን በጽኑ ይሞግታሉ።

ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰብ በታሪክ፣ በሕግ እና በሕዝብ አሰፋፈር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ የባሕር በር መሆኗን ያምናል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር መዘጋት እንደ ዓድዋ ወይም የማይጨው ጦርነት ሁሉ ትልቅ ሀገራዊ ትርጉም ያለው ክስተት ነው። ኤርትራ በ1983 ዓ.ም በጦር ሠራዊት ኃይል ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች በኋላ የኢትዮጵያ የባሕር በር መዘጋት፣ ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ ያሳዘነ እና ያስቆጣ፣ ለዘመናት ሁሉም በየቤቱ የቆዘመበት፣ አሁን ደግሞ አጀንዳውን መንግሥት ወደ አደባባይ ካመጣው በኋላ የባሕር በር ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው የብሔራዊ ጉዳይ ሆኗል።

አሰብ ለኢትዮጵያ ያላት ቅርበት እና ታሪካዊ ትሥሥር፣ አካባቢው የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ መተንፈሻ መሆኑን በዓለም አቀፍ የሕግ መርሆች ጭምር (እንደ "Vital Interest" እና ታሪካዊ ባለቤትነት) ሊሞገት የሚችል አቅም አለው።

በፌዴሬሽን ዘመንም ሆነ በፍጹም አንድነት ጊዜ፣ ኢትዮጵያውያን በኤርትራውያን ላይ ምንም ዓይነት በደል እንዳልፈጸሙ እና የነበረው የጋራ ታሪክ የባሕር በሯን የጋራ የማድረግ ሥነ-ልቦናዊ መሠረት ያለው መሆኑን አምባሳደር ዘውዴ በመጽሐፋቸው አስምረውበታል።

የ"የየብስ ተከል ሀገር"ነት (Landlocked) ኢኮኖሚያዊ ስብራት

አንድ ሀገር "የየብስ ተከል" (Landlocked) መሆን በኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ እጅግ አውዳሚ ነው።

የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ የየብስ ተከል ሀገራት ከዓለም አቀፍ ንግድ ጋር ለመተሣሠር የሚያወጡት የሎጂስቲክስ እና የትራንስፖርት ወጪ የባሕር በር ካላቸው ሀገራት አንጻር እስከ 50 በመቶ ብልጫ አለው።

ይህ ደግሞ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) ከማዳከሙም በላይ፣ የሀገራትን ተወዳዳሪነት ገደል ውስጥ ይከትተዋል። ይህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ የሚያሳየው በኢትዮጵያ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ሁኔታ መፈፀሙን ነው።

ዶክተር ያዕቆብ በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት በመሆኗ ምክንያት በቀን ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ እና የአገልግሎት ክፍያ ትከፍላለች።

ይህ በየዓመቱ የሚከፈለው እና ውኃ እንደበላው የሚቆጠረው ከፍተኛ ገንዘብ፣ ድህነትን ለመቅረፍ ሊረዱ ይችሉ የነበሩ ኃያ እና ሰላሳ ፋብሪካዎችን ለመገንባት፣ ወይም ሰፊ ለሆነ መሠረተ ልማት ግንባታ ሊውል ይችል የነበረ የሕዝብ አንጡራ ሀብት ነው።

የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሕዝብ ቁጥር መጨመር (ከ130 ሚሊዮን በላይ)፣ አሁን ባለው የየብስ ተከልነት ሁኔታ ፈጽሞ ሊቀጥል አይችልም። የነጻ ንግድ ቀጣናዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ግዙፍ የግብርና ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ በተወዳዳሪ ዋጋ ለመግባት፣ የራስ የሆነ እና ሉዓላዊነቱ የተረጋገጠ የባሕር በር ማግኘት የቅንጦት ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው።

የቀይ ባሕር የጂኦፖለቲካዊ ፉክክር፣ የኃያላን ርብርብ እና ማኅበራዊ ትሥሥር

ቀይ ባሕር በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጡ የዓለም የደም ሥር ነው። በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ቶን ሸቀጥ፣ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት እና የኮንቴይነር እንቅስቃሴ የሚያልፈው በዚህ ጠባብ የውኃ መስመር ነው።

የኃያላን ወታደራዊ ፉክክር፦ ዛሬ ቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ የዓለም ኃያላን ሀገራት የጦር ሰፈር የገነቡበት እና ጡንቻቸውን የሚለካኩበት ቀጣና ሆኗል። እነዚህ ኃያላን ሀገራት ቀይ ባሕርን መቆጣጠር ዓለም አቀፍ የንግድ መስመርን እና የኢነርጂ ደኅንነትን መቆጣጠር መሆኑን በሚገባ ተረድተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ግዙፍ የሕዝብ ብዛት እና ወታደራዊ አቅም እያላት፣ ከቀይ ባሕር መነጠሏ በቀጣናው የደኅንነት ፖለቲካ (Security Architecture) ላይ ሊኖራት የሚገባውን የተፈጥሮ ሚና አሳጥቷታል።

ከፖለቲካ እና ከኢኮኖሚ ባሻገር የቀይ ባሕር ባለቤትነት ጥያቄ ማኅበራዊ ፋይዳ አለው። የቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ታሪካዊ አንድነት እና ኢትዮጵያዊነት ሊካድ የማይችል ሐቅ ነው። ድንበር አቋራጭ የሆኑት ባህላዊ፣ ቋንቋዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ትሥሥሮች፣ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ጋር ለዘመናት ያቆራኙ የተፈጥሮ ገመዶች ናቸው።

የሆርሙዝ ሰርጥ ቀውስ እና የቀይ ባሕር አዲስ የስትራቴጂካዊ ከፍታ

በቅርቡ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በተለይም በእስራኤል-አሜሪካ ጥምረት እና ኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት የሆርሙዝ ሰርጥን (Hormuz Strait) የደኅንነት ሥጋት ውስጥ ጥሎታል።

የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ወይም አደጋ ላይ መውደቅ፣ የዓለምን የነዳጅ ማጓጓዣ አማራጮች ያጠብባቸዋል። በዚህ ጊዜ፣ ቀይ ባሕር እና ባብ-ኤል-መንደብ (Bab-el-Mandeb) ብቸኛ እና እጅግ ወሳኝ የዓለም የኢነርጂ እና የንግድ ደም ሥር ሆነው ብቅ ይላሉ።

ይህ ዓለም አቀፋዊ የጂኦ-ስትራቴጂካዊ ለውጥ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ይበልጥ ምክንያታዊ ያደርገዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቀይ ባሕር ላይ አስተማማኝ፣ ሰላማዊ እና ጠንካራ አጋር ሀገር ይፈልጋል።

ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር እና በባሕሩ ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጠብቅ የባሕር ኃይል ተመሥርቶ መንቀሳቀስ ቢጀምር ኖሮ፣ የራሷን የነዳጅ አቅርቦት ደኅንነት ከማረጋገጥ አልፋ፣ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን ሰላም በማስከበር በኩል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ እና ስትራቴጂካዊ የበላይነትን ትቀዳጅ ነበር።

የዓለም የኢነርጂ ገበያ በተናወጠ ቁጥር፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የየብስ ተከል ሀገራት ቀዳሚ ገፈት ቀማሾች ናቸው። በመሆኑም የባሕር በር ባለቤትነት፣ ለውጭ ጫና እና ለገበያ መናወጥ የማይበገር (Resilient) ኢኮኖሚ ለመገንባት ዋነኛው መፍትሔ ነው።

የቀይ ባሕር ባለቤትነት የ"ትውልድ ተልዕኮ" ነው

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የታሪክ ናፍቆት (Nostalgia) አይደለም፤ የፍትሕ፣ የሕግ፣ የኅልውና እና የልማት ጥያቄ ነው። የዶክተር ያዕቆብ እና የአምባሳደር ዘውዴ ረታ ሥራዎች እንደሚያስገነዝቡን፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር የተዘጋው በሕዝቦች ፍላጎት ሳይሆን በተሳሳቱ ውሎች፣ በቅኝ ግዛት መዘዞች እና በወቅቱ በነበሩ የዲፕሎማሲ ክፍተቶች ነው።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን መረዳት ያለባቸው ትልቁ እውነት፤ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በፖለቲካ የተረጋጋች እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያላት ሀገር ለመገንባት የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ የግድ መሆኑን ነው።

ሚሊዮኖች የሚራቡባት፣ ሥራ አጥነት የነገሠባት ሀገር፣ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለወደብ ኪራይ እየገበረች ማደግ አትችልም።

ስለሆነም፣ አሁን ያለው እና መጪው የኢትዮጵያ ትውልድ ይህንን ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊነት የማረም ኃላፊነት አለበት። የባሕር በር ማግኘት የትውልድ ተልዕኮ ነው።

ኢትዮጵያ የየብስ ተከልነትን ሰንሰለት በጥሳ፣ የተፈጥሮ መተንፈሻዋ ወደሆነው ቀይ ባሕር መመለሷ ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም፣ ለዓለም አቀፍ ንግድ ደኅንነት እና ለሕዝቦቿ የኢኮኖሚ ነጻነት ብቸኛውና ትክክለኛው መንገድ ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

#EBC #Ethiopia #Seaaccess #RedSea #NomoreLandlocked