Search

ትችት ያልበገራቸው እናት ከልጃቸው ጋር እኩል በዲግሪ ተመረቁ

እሑድ መጋቢት 13, 2018 51

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የ14ኛው ዙር የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ አንድ ልዩ ታሪክ ተመዝግቧል። እናትና ልጅ፣ በአንድ መድረክ፣ በአንድ የትምህርት ዘርፍ፣ በአንድ ቀን እኩል በመመረቃቸው የዕለቱን ድምቀት ጨምረውታል።
ወይዘሮ ትግስት ታከለ እና ልጃቸው ሰላማዊት ተድላ፣ ሁለቱም በማኔጅመንት ትምህርት ዘርፍ በዲግሪ ተመርቀዋል። የወይዘሮ ትግስት ህልም ልጃቸው ተምራ ተመርቃ ማየት ብቻ ሳይሆን፣ "ለእውቀት ዕድሜ ገደብ የለውም" የሚለውን መርህ በተግባር ማሳየትም ነበር።
ልጃቸውን ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ ሲያበረቷት የነበሩት እናት፣ ዛሬ ግን ከኋላዋ ሆነው የምርቃት ፎቶ እያነሷት ሳይሆን፣ አብረዋት የክብር ካባ ለብሰው ጎን ለጎን ቆመዋል።
ከልጃቸው ጋር መማራቸው ቀላል አልነበረም። "በዚህ ዕድሜ ተምረው የት ሊደርሱ ነው?" የሚሉ የሰላ ትችቶችና የማያስደስቱ ዕይታዎች ቢገጥሟቸውም፣ ወይዘሮ ትግስት ጆሮዋቸውን ለወሬ ሳይሆን ለመምህሮቻቸው ምክር ሰጥተው በስኬት ተመርቀዋል።
ሰላማዊትም እናቷ አብረዋት መማራቸው ጊዜዋን በአግባቡ እንድትጠቀምና ከአልባሌ ቦታ እንድትቆጠብ እንዳደረጋት ገልጻለች።
ይህ የእናትና ልጅ ጉዞ እዚህ ጋር አያበቃም። የማኔጅመንት እውቀታቸውን ይዘው የራሳቸውን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቁርጠኛ ናቸው። በተጨማሪም ያልተቋረጠው የእውቀት ጥማታቸውም ወደ ሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) ያመራቸዋል።
ወይዘሮ ትግስት በምርቃቱ ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሰላም ከራስ እንደሚጀምርና ትውልዱ ሰላምን በማጽናት ለሀገር ዋልታ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
የወይዘሮ ትግስት እና የሰላማዊት ታሪክ፣ ዓላማ ካለ ዕድሜ ቁጥር ብቻ መሆኑን፣ ፍቅርና ትምህርት ደግሞ ትውልድን በአንድ መድረክ ላይ አቀንቅነው ለድል እንደሚያበቁ ያስተምረናል።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ ያስመረቀው 1 ሺህ 254 ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት የታነጸ ቤተሰብንና ተምሳሌት የሚሆን ጽናትንም ጭምር ነው።
በላሉ ኢታላ