“መጀመሪያ አካባቢ እውነታውን መቀበል ከብዶኝ ነበር፤ በቃ እኔ ምንም ነገር ማድረግ እንደማልችልና ዋጋ እንደሌለኝ አስብ ነበር።”
ይህ በአንድ ወቅት በተስፋ መቁረጥ ይደመጥ የነበረ የታዳጊ ወጣት ድምፅ፣ ዛሬ በደስታና በስኬት ተቀይሮ “በሕይወቴ ደስተኛ የሆንኩበት ቀን ያ ቀን ነው” ወደሚል የምስጋና ዜማ ተለውጧል።
ይህ አስገራሚ የሕይወት ለውጥ በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፤ በዝምታ፣ በትህትና እና በጽናት በሚሠሩት የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የእናትነት አሻራ የተገኘ ውጤት ነው።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለሀገራቸው እና ለወገናቸው ያላቸው ተቆርቋሪነት ከመደበኛ የኃላፊነት ወሰን በላይ መሆኑን በተግባር አስመስክረዋል።
እናትነትን በቤት ወስነው ሳይቀሩ፣ የሌሎችን ሕመም እና ጉድለት በመጋራት በመላ ኢትዮጵያ 37 ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት ለ40 ሺህ በላይ ወጣትች ተስፋ ሆነዋል።
ከነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶች መካከል በልዩ ትኩረት የሚጠቀሰው "ብርሃን የዓይነ ስውራን 2ኛ ደረጃ አዳሪ ት/ቤት" አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ድንቅ ሥራ ነው።
ዓይነ ስውራን ተማሪዎች ቀደም ሲል ይገጥሟቸው የነበሩ መሰናክሎች እጅግ መራራና ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ።
ለዓመታት በአስቸጋሪ መንገዶች ላይ ኪሎ ሜትሮችን በእግር ሲጓዙ፣ የሚያደናቅፏቸው እንቅፋቶች እና ጉድጓዶች በአካላቸውና በሥነ-ልቦናቸው ላይ ጠባሳ ጥለውባቸው አልፈዋል።
በአካታች ትምህርት ስም ከሌሎች ጋር ሲማሩም “ይህ ላንቺ አይሆንም፣ አትችይም” የሚሉ ቅስም ሰባሪ ቃላትና በቴክኖሎጂ (ICT) ክፍሎች የሚደርስባቸው መገለል የዕለት ተዕለት ገጠመኛቸው ነበር።
ዛሬ ግን ያ የጨለማ ታሪክ ተቀይሮ ብርሃን ሰፍኗል። ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ለማስተማር የተከፈተው ብርሃን የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት እነዚህን ተማሪዎች ከመላው ኢትዮጵያ ሰብስቦ በአንድ ጥላ ስር አቅፏቸዋል።
ተማሪዎቹ ትምህርት ቤታቸውን በኩራት “ትንሿ ኢትዮጵያ” ብለው ይጠሩታል። ይህ ስያሜ የአራቱም አቅጣጫ ልጆች በዘርና በቋንቋ ሳይገደቡ በአንድነት የሚማሩበት፣ የሚኖሩበትና የወደፊት ኢትዮጵያን ተስፋ የሚሰንቁበት ማዕከል መሆኑን ያሳያል።
ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎቹ ከመደበኛ የትምህርት ገበታነት ባለፈ እንደ ሁለተኛ ቤት ሆኖ ያገለግላል። ተማሪዎቹ እንደሚመሰክሩት፤ ተቋሙ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጁ የብሬል ፕሪንት ማሽኖች፣ የአይሲቲ ላቦራቶሪዎች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎችና የክሊኒክ አገልግሎቶችን አካትቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ንጹህ የመኝታ፣ የሻወርና የምግብ አገልግሎቶች መሟላታቸው ተማሪዎቹ ትኩረታቸው በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲሆን አስችሏቸዋል።
የቀዳማዊት እመቤቷ ያልተቆጠበ ጥረትና የተማሪዎቹ ጠንክሮ መሥራት ፍሬ ማፍራቱን ያረጋገጠው ደግሞ በቅርቡ የተመዘገበው አስደናቂ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤታቸው ነው።
በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተፈተኑ 57 ተማሪዎች መካከል 56ቱ (ማለትም ከ98 በመቶ በላይ) ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችል ውጤት በማምጣት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የማሳለፍ ምጣኔ ካላቸው ትምህርት ቤቶች ተርታ ተሰልፏል።
ይህ ውጤት አካል ጉዳተኝነት ለስኬት እንቅፋት እንዳልሆነ እና ዕድሉ ከተመቻቸ የማይታለፍ ፈተና እንደሌለ ያረጋገጠ ትልቅ ማስረጃ ነው።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የከተቡት ይህ የእናትነት አሻራ በሺዎች የሚቆጠሩ ልበ ብርሃኖች ተስፋ እንዲያዩና ለሀገራቸው የሚተርፉ ዜጎች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
በላሉ ኢታላ
#Ethiopia #Education #FirstLady #ZinashTayachew #EBC