በመላው ሀገራችን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
መንግሥት በትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ስትራቴጂካዊ ተግባራት መካከል የመሠረታዊ ትምህርት ዋነኛው ሲሆን፣ ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ከለውጡ በፊት የነበረው አሰራር በከተሞች ላይ ብቻ ያተኮረና አቅም ያላቸው ወላጆች ብቻ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩባቸው ጥቂት ትምህርት ቤቶች የነበሩ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ተቀርፎ የትምህርት ቤቶቹ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ተደርጓል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ በመላ ኢትዮጵያ 34 ሺህ የሚሆኑ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተደራሽ ባልሆኑባቸው ወረዳዎች ሁሉ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በታቀደው መሠረት፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
ይህ ተደራሽነት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ፍትሐዊ የትምህርት ተጠቃሚ ለማድረግና በዕውቀት የዳበረ ቀጣይ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ብሔራዊ ጥረት ውስጥ የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስገንዝበዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ