በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ ትምህርት የጨለማ መግፈፊያና የሀገር ዕድገት ማሳለጫ ዋነኛው መሣሪያ መሆኑን በተግባር ለመተርጎም የቆረጠው የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በመላ ኢትዮጵያ የፈነጠቀው የብርሃን ጮራ ለብዙ ሺህ ተማሪዎች አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ከፍቶላቸዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ትኩረቱን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በማድረጉ፣ በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች ተማሪዎች ከአንደኛ ደረጃ በኋላ በትምህርት ቤት ርቀት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡበትንና ለተለያዩ ጥቃቶች የሚጋለጡበትን እንግልት ቀርፏል።
ዛሬ ተማሪዎች በትውልድ መንደራቸው ዘመናዊ ትምህርት የማግኘት ዕድል በማግኘታቸው በርቀት ምክንያት የሚያጋጥመው እንግልት አብቅቶ የዕውቀት ማዕከላት ተከፍቶላቸዋል።
ጽሕፈት ቤቱ የገነባቸው 35ቱ ትምህርት ቤቶች ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎችን፣ የሳይንስ ቤተ-ሙከራዎችን፣ ቤተ-መጽሐፍትንና ንጹህ የመጠጥ ውኃን ያሟሉ የዕውቀት ማዕከላት ናቸው።
ለየት ባለ መልኩም ለአካል ጉዳተኞች እና ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትኩረት በመስጠት በአዲስ አበባ የዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ምቹ የትምህርት ከባቢን ፈጥሯል።
ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚሆን የገንዘብ ምንጭ የተገኘው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የ"መደመር" መጽሐፍ ሽያጭ እና ከበጎ አድራጊዎች በተሰበሰበ ድጋፍ መሆኑ፣ በዝቅተኛ ወጪና በአጭር ጊዜ ጥራት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚቻል ለሌሎች ተቋማት ታላቅ የሥራ ባሕል ተምሳሌት ሆኗል።
ይህ የልማት ጉዞ በመላ ኢትዮጵያ ተደራሽ በመሆን ትምህርት ቤቶቹ በተገነቡባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎችን የትምህርት ጥም ማርካት ችሏል።
በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገነቡት 35 ትምህርት ቤቶች ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች በምቾት ተምረው ለትልቅ ደረጃ እንዲበቁ መሠረት የጣሉ ሲሆን፣ ጽሕፈት ቤቱ አሁንም ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የነገዋን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት በትጋት መስራቱን ቀጥሏል።
በላሉ ኢታላ