Search

አፋር የተፈጥሮ ድንቃድንቅ የታደለች የምድራዊ ገነት መገኛ ናት፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

እሑድ መጋቢት 13, 2018 83

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፋር ክልል የሚገኘውን ልዩ የተፈጥሮ ጸጋና የለመለመ ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ምርቃት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ክልሉ በታሪክና በተፈጥሮ የታደለ መሆኑን ገልጸዋል።
ጥቅጥቅ ብሎ የበቀለውና ለየት ያለ ቅርጽ ያለው የፓልም ጫካ፣ በአካባቢው የሚፈሰው የተፈጥሮ ፍልውኃ፣ ውብ ተራራዎችና ልዩ የሳር ዝርያዎች ለሺህ ዓመታት የቆዩ ድንቅ ሀብቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህን የተፈጥሮ ምስጢሮች ለዓለም ለማስተዋወቅና የሰዎችን "ዓይን ለመግለጥ" የ‘ገበታ ለትውልድ’ ፕሮጀክት በአካባቢው መገንባቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ በአካባቢው ያሉትን እንደ አሰቦትና አዋሽ ያሉ ታላላቅ ፓርኮች ካላቸው የሳፋሪ አቅም አንጻር በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከአዳማ አዋሽ የሚገነባው የፍጥነት መንገድ ሲጠናቀቅና የአዳማ አዋሽ የባቡር መስመርን ጨምሮ፣ ማንኛውም ሰው ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሁለት ሰዓት የጉዞ መንገድ እነዚህን ድንቆች ማየት እንደሚችል ተናግረዋል።
በተለይም አዲሱ የቢሾፍቱ ኤርፖርት ሲገነባ ጉዞው ይበልጥ አጭርና ምቹ እንደሚሆን በመጠቆም፣ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ጎብኚዎች በእንደዚህ ዓይነት የተፈጥሮ ድንቆች የመዝናናት ዕድል እንዲያገኙ አልማዝ የሆኑ መዳረሻዎችን ማልማት የብልጽግናችን አካል ነው ብለዋል።