የአፋር ክልል መንግሥት ከሰመራ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን እና ስምንት ዓይነት የውኃ ቀለማት ያሉትን አላሎባድ የቱሪስት መዳረሻ በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት መወሰኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ለሰው ዘር መነሻ በሆነችው እና በተፈጥሮ ሀብት በታደለችው አፋር ምድር የተገነባው ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ለክልሉ ሕዝብ የላቀ ክብር መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አንድ ታዋቂ ሼህ ለዘመዳቸው የሰጡትን ምክር በማስታወስ፣ እውነተኛ ስኬት እና በረከት የሚገኘው ለመልካም ሥራ ጊዜን በመስጠት እና ላብን አፍስሶ በመሥራት መሆኑን ጠቁመዋል።
ላብ ሳይደርቅ የሚደረግ ጥረት እና ጸሎት በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው በማንሣትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንኑ የልፋት እና የጥረት ውጤት በተግባር ለሀገር እያበረከቱ መሆናቸውን አድንቀዋል።
እውነተኛ ሐውልት ማለት ድንጋይ መቆለል ሳይሆን ለሕዝቡ የሚተርፍ እና ትውልድ የሚጠቀምበት ሥራ መሥራት መሆኑን ያነሡት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የኒዒን ፕሮጀክትም የአፋርን የቱሪስት መዳረሻነት የሚያጎላ እና ለሕዝቡም የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።
የክልሉ መንግሥትም ይህን የልማት ጉዞ በማስቀጠል አላሎባድ የቱሪስት መዳረሻ በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት መወሰኑን ነው የገለጹት።
የተለያዩ ተቋማት ሥራዎቻቸውን እና ስብሰባዎቻቸውን ከአዲስ አበባ ወጣ በማድረግ እንደ አፋር ባሉ ምቹ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
"ሁሉም ሰው ፕሬዚዳንት መሆን ባይችልም እንደ ፕሬዚዳንት ሆኖ ሊሠራ እና ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል" በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በልማት ረገድ ትልቅ ኃላፊነት መወጣታቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ቀሪው ሥራ የሁሉም ኃላፊነት በመሆኑ እያንዳንዱ “የሉሲ ተወላጅ” አሻራውን ማሳረፍ እንዳለበት አሳስበዋል።
የአፋር ሕዝብም ይህን ፕሮጀክት የመጠበቅ እና እንግዶችን የማስተናገድ ድርሻውን በከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #AfarRegion #NeeleProject #TourismEthiopia #Development #EthiopianBroadcastingCorporation #EBC