የኒዒን ፓልም ሎጅ የአፋርን ተፈጥሯዊ መስህቦች እና ባህላዊ እሴቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ ታላቅ አቅም ያለው መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኢ/ር መሐመድ አብዱራህማን ገለጹ።
ይህ ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻ ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 222 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በ138 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።
ፕሮጀክቱ ያካተታቸው ዋና ዋና መሠረተ-ልማቶች፦
✅ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች - በአካባቢው የሚገኙ የፍል ውኃ ምንጮች እና የዘንባባ ዛፎችን የጠበቀ ልማት)፤
✅ ሰው ሠራሽ ሐይቅ - ከ6 ሔክታር በላይ መሬት የሚሸፍን ውብ ሐይቅ፤
✅ የአየር ትራንስፖርት - ሁለት የሔሊኮፕተር ማረፊያ (Helipads)፤
✅ መሠረተ-ልማት - የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእንግዳ ማረፊያ ሕንጻዎች፣ የስብሰባ አዳራሽ እና የምግብ አዳራሽ፤
✅ የውኃ አገልግሎት - የምንጭ ውኃን አጣርቶ ለሎጁ አገልግሎት የሚያውል ዘመናዊ የማጣሪያ ጣቢያ ተካትተውበታል።
ኢ/ር መሐመድ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ከቱሪዝም ባለፈ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንፁህ የመጠጥ ውኃ ማበልጸጊያንም ያካተተ ነው።
"የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ሀገራችን በአስደናቂ ታሪኳ፣ በተለያዩ መልክዓ-ምድሮቿ እና ኅያው ባህሏ የጉዞ መዳረሻ ሆና ይበልጥ እንድትደምቅ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ" ብለዋል ኢ/ር መሐመድ።
ለፕሮጀክቱ ስኬት ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም አሻራቸውን ላኖሩ መሐንዲሶች፣ ባለሙያዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።
በዮናስ በድሉ
#EBC #Ethiopia #Afar #tourism