የአፋር ክልል ለኢትዮጵያ ኅልውና እና ለሰው ዘር ሥልጣኔ ያለው ፋይዳ ከጥንታዊነትም ባሻገር በጥልቅ የታሪክ አሻራዎች የተሣሠረ ነው።
“የሰው ዘር መገኛ” ተብሎ በሚታወቀው አፋር የ3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያላት “ሉሲ” (ድንቅነሽ) መገኘቷ ክልሉን የዓለም የሳይንስ እና የባህል ማዕከል ያደርገዋል።
የአፋር ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የራሱ የሆነ ‘ማድዓ’ የተሰኘ ባህላዊ የሕግ ሥርዓት ያለው እና ሉዓላዊነቱን አስከብሮ የኖረ ኩሩ ሕዝብ ነው።
ይህ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት የከፈለው የደም መሥዋዕትነት በታሪክ መዝገብ በደማቁ ተጽፏል።
በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን በወርነር ሙንዚንገር የተመራውን የግብፅ ወራሪ ጦር እ.አ.አ. በ1875 ዓ.ም በአውሳ በረሃ ላይ በመደምሰስ የኢትዮጵያን ድንበር ያስከበረው የአፋር ጀግኖች ተጋድሎ፣ ለጠላት የማይበገር ፅኑ ኢትዮጵያዊነት ማሳያ ነው።
በታላቁ የዓድዋ ድል ወቅት በሱልጣን መሐመድ ሀንፈሬ (ኢላታ) መሪነት፣ የአፋር ተዋጊዎች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን የኢጣሊያን ወራሪ ጦር በመመከት ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
በሁለተኛው የፋሺስት ወረራ ወቅትም እንደ ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ ያሉ ታላላቅ መሪዎች ለሀገራዊ አንድነት የከፈሉት መሥዋዕትነት እና ያሳዩት ፅናት፣ የአፋር ሕዝብ የኢትዮጵያ የድንበር ጠባቂ እና የኅልውናዋ ምሰሶ መሆኑን ያረጋግጣል።
አፋር በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ምድር ቢሆንም፣ ለዘመናት ይህ እምቅ አቅም ለሕዝቡ ብልጽግና ሳይውል መቆየቱ የሚያስቆጭ የታሪክ አጋጣሚ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን የታሪክ እውነታ ሲገልጹ፣ “መሠራት የነበረበት የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ነበር፤ አሁን ስለዘገየን አንቆጭም” ብለዋል።
ክልሉ የዓለምን የግብርና ምርታማነት ሊቀይር የሚችል ግዙፍ የፖታሽ ክምችት፣ የጨው ማዕድን፣ ቤንቶናይት (ተዓምራዊው ጭቃ) እና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ በርካታ ማዕድናት ባለቤት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከአዋሽ ወንዝ የሚገኘው የውኃ ሀብት፣ በመሬት ውስጥ ያለው የጂኦተርማል (የእንፋሎት ኃይል) እንዲሁም የፀሐይ ብርሃን እምቅ አቅም ክልሉን የኢትዮጵያ የኢነርጂ እና የግብርና ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ቢሆንም ለረጅም ጊዜ ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል። ይሁን እንጂ አሁን በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው የልማት እንቅስቃሴ ይህንን የታሪክ መዛባት በመቀየር ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረጹት የዘላቂ ልማት ራዕይ የአፋርን የተፈጥሮ ፀጋዎች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመቀየር የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው።
የአፋር በረሃዎች ዛሬ የስንዴ አምራች ወደ መሆን ተሸጋግረዋል። ሆድ ብሶት በሚመስል መልኩ በየክረምቱ በቁጣ ሁሉን ሲጠራርግ የኖረው አዋሽ አሁን ተገርቶ አፋርን የበረሃ ገነት እያደረጋት ይገኛል። በክልሉ እየተካሄደ ያለው የክረምት ስንዴ ልማት የአፋርን መሬት ወደ ምርታማነት ቀይሮታል። በዱብቲ ወረዳ ብቻ በ8 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የስንዴ ልማት፣ አፋር ከከብት እርባታ ባለፈ የሀገራችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚችል እምቅ አቅም እንዳለው በተግባር ያሳየ ነው።
እነዚህ የልማት ሥራዎች ከአፋር ቤንቶናይት ማዕድን ፋብሪካ እና ከሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ጋር ተዳምረው ክልሉን የኢንዱስትሪ እና የንግድ ማዕከል እያደረጉት ይገኛሉ። በዚህ አዲስ የልማት ምዕራፍ ውስጥ ሌላው እጅግ ደማቁ እና ተስፋ ሰጪው ክስተት በ“ገበታ ለትውልድ” መርሐ-ግብር የተገነባውና በታላቅ ድምቀት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው “ገነት ኒዒን ሌ” (Genet Ni'in Le) ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ ነው።
ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ክትትል የተገነባው ይህ ድንቅ የቱሪስት መዳረሻ፣ የአፋርን ውብ መልክዓ ምድር፣ የተፈጥሮ ፍልውኃዎች እና ለምለም የዘንባባ ዛፎችን በማጣመር የተገነባ የኢትዮጵያ አዲስ የቱሪዝም ተምሳሌት ነው።
ይህ ሎጅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ የተገነባ ሲሆን፣ በቅርበት ከሚገኘው የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ እና ፏፏቴ ጋር ተዳምሮ ለክልሉ የቱሪዝም ዕድገት አዲስ የኢኮኖሚ ምንጭ ይሆናል። ሎጁ ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ የአፋርን ባህላዊ እሴት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ አቅም ይዞ ብቅ ብሏል።
የአፋር ጥንታዊነት እና ፅኑ ኢትዮጵያዊነት ዛሬ በልማት እና በብልፅግና ታጅቦ አዲስ ታሪክ እየጻፈ ነው። የኒዒን ሌ ፓልም ስፕሪንግ ሎጅ መከፈት እና እየተስፋፋ ያለው የተቀናጀ ልማት የአፋር ሕዝብ ከተፈጥሮ ሀብቱ ተጠቃሚ የሚሆንበት እና ኢትዮጵያ ያላትን የኢኮኖሚ አቅም የምታጠናክርበት የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ይህ ግን ዓይን ከፋች ጅማሮ እንጂ ፍጻሜ አይደለም። አፋር በምድሯ የተሸከመችው ሀብት፣ በኢትዮጵያዊነቱ ለማይደራደረው ሕዝቧ በሚመጥን መልኩ ይለማል።
ኢትዮጵያን በደሙ ያቆማት የአፋር ሕዝብ ልዕልናውን የሚመጥን ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ጉዞ አታቆምም። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው “በዚህ ብቻ ሳንረካ፣ ሩጫችን ገና ረጅም መሆኑን እና አፋር ገና ያልተነካ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን ጅማሮ ይበልጥ በማላቅ ለማስቀጠል እንተጋለን!” ያሉት።
በለሚ ታደሰ
#EthiopiaRising #Afar #NiinLeeLodge #DineForGeneration #LandOfOrigins