Search

ባለ ወደብዋ ኢትዮጵያ

ማክሰኞ መጋቢት 15, 2018 991

የታሪክ፣ የጂኦ-ፖለቲካ እና የብሄራዊ ጥቅም ትስስር

ወደብ አልቦነት የኢትዮጵያ ፍጥረተ ማንነት አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ከወደብ ሳትነጠል ከውሀ ዳርቻዎች ሳትርቅ ዘመናትን ተሻግራለች፡፡ አዱሊስ ላይ አክሱማውያን በወቅቱ ገናና ከነበሩ ግሪካዊያንና ባዛንታይን ነገስታት ለመገናኘትና የእጣን፣የወርቅ ፣የከበሩ ድንጋዮች፣ የአደን ዱር አራዊት ቆዳ ምርቶቻቸውን ይለዋወጡና ይሻሻጡ ነበር፡፡

በዚህ ንግድ  ባገኙት ሀብትና አቅም የላቀ ስልጣኔን ብቻ ሳይሆን የዳበረ ባህር ኃይል ገንብተው  ቀይ ባህርን ተሻግረው የመንንና ደቡብ አረቢያን ይቆጣጠሩ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

8ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የቤጃ ህዝቦች ምጽዋን አካባቢው ሙሉ ለሙሉ በኦቶማን ቱርኮች ቁጥጥር ስር እስኪወድቅ ድረስ እንደ ንግድ ማዕከልነት ይጠቀሙበት ነበር፡፡

በኋላም በኦቶማን ቱርክ እንቅፋት የተፈጠረባቸው የኢትዮጵያ ነገስታት ፊታቸውን ወደ ህንድ ውቅያኖሷ ዘይላ በማዞር በአዳል ህዝቦች አማካኝነት ዘይላን የኢትዮጵያ ዋና ወደብ ማድረጋቸው ታሪክ ያነሳል፡፡

18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ቦታዎች ማለትም  የዛሬዋ ሶማሌላንድ 2 ከተማ በርበራና በጊዜው በፈንሳይ ኩባንያ ስር የነበረው የአሁኑ ሰሜናዊ ጅቡቲ የወደብ ከተማ ታጁራ ለኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

ዳግማዊ ምኒሊክ ከፈረንሳይ ጋር ባደረጉት ስምምነት የቀድሞዋን ኦቦክ መንደር ሁዋላ ጅቡቲ የተሰኘችውን  የኢትዮጵያ ዋና ወደብ በመሆኗም የባቡር መስመር ሳይቀር እንዲገባ ተደረገ፡፡

ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ በባሮ ወንዝ ላይ የሚገኘውን የጋምቤላ ወደብ እንግሊዞች ሲጠቀሙበት እንደነበር አስተውለው የጅማውን ንጉስ አባ ጅፋርን በቅርብ እንዲቆጣጠሩትና የሚጠቀሙበትም ነገር ካለ እንዲጠቀሙ ሀላፊነቱን ሰጧቸው።

አባ ጅፋር ቡና የዝሆን ጥርስ እና የዱር እንስሳት ቆዳ በዚህ ወደብ ተጠቅመው ለእንግሊዞቹ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ነበር።

አሰብ ማናት? ምንድን ናት?

የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ ከመደበኛ የንግድ መውጫና መግቢያነት ባለፈ፣ ከአገሪቱ ህልውና፣ ታሪክ እና ስነ-ልቦና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ስፍራ ነው። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ የአሰብ ጉዳይ በፖለቲካዊ ውይይቶች፣ በኢኮኖሚ ስሌቶች እና በጂኦ-ፖለቲካዊ ትንታኔዎች ግንባር ቀደም ሆኖ ይገኛል።

ቀደም ሲል አሰብ  በደቡባዊ ቀይ ባህር ጫፍ የሚገኝ አፋሮች ከባህር ማዶ ካሉት የየመን ሐድራሙት ጎሳዎች ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ስፍራ ነበር።

1830 እራሱን የካቶሊክ ቄስ ነኝ ብሎ የሚጠራ በሁዋላ ግን ብዙዎች ካህንነቱን የሚጠራጠሩት ጁሰፔ ሳፔቶ የተባለ ኢጣልያዊ ባካባቢውና በሰሜን ኢትዮጵያ ከመጣ ጀምሮ  ለተለያዮ የኢጣልያ ኩባንያዎች እንደ ወኪል ሆኖ መሬት በመግዛት ተጠምዶ ነበር።

 በዚህም መሰረት ነበር በጊዜው የአዳል (አፋር) ስልጣን ከነበሩት ስልጣን ኢብራሒም አሰብንና አካባቢውን የገዛው።

ኢጣልያ ባካባቢው አነስተኛ የጦር ሀይል ከማስፈር በስተቀር እምብዛም በወደብነት ይህንን ቦታ እስከ ሁለተኛው የአለም ጦርነት ዋዜማ ድረስ ተጠቅማበት አታውቅም። ኢጣልያ ኢትዮጵያን ስትወር ግን ሙሶሎኒ ወደቡን መጠነኛ ጥገና አድርጎ የጦር መሳርያ ለማስገባት ተጠቅሞበታል።

ቆይቶም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ስትቀላቀል ቀዳማዊ ሀይለስላሴ "የወደብ አስተዳደር መስርያ ቤት" በሚል ተቋም አቋቁመው አሰብ ወደብን የወደብ ቁመና እንዲይዝ ስራው ተጀመረ።

ይሁንና 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ይከናወን የነበረው በምጽዋ ወደብ ነበር። የአሰብ መሰረተ ልማት እጅግ በተሻለ መልኩ የተገነባውና የወደብ ከተማነቱ የጎላው በወታደራዊው ደርግ መንግስት ነበር። ምጽዋ በጊዜው እየተፋፋመ በመጣው ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ ለጥቃት የተጋለጠ በመሆኑ አሰብ ከአማራጭ ወደብነት አልፎ ወደ ዋና ወደብነት እየተሸጋገረ ነበር።

በደርግ መንግስት ዘመን አሰብ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፍያ፣ መንገዶች እና ዘመናዊ መኖርያ ቤቶች ተሰሩለት።በቦታው በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዘመን ስራ ጀምሮ የነበረው በሶቭየት ህብረት እርዳታ የተገነባው ነዳጅ ማጣርያ ስራውን አጠናክሮ ቀጥሎ ድፍድፍ ነዳጅ እያጣራ ወደ መሀል ሀገር ይልክ ነበር። አሰብ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከመሀል ሀገር ሄደው የሚኖሩበትና ቦታ ሆና ነበር።

በ1980 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 1987) የወጣው አዲሱ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት አገሪቱን በ5 ራስ-ገዝ እና በ24 አስተዳደር አካባቢዎች ሲከፍል፣ አሰብ አንዷ ራስ-ገዝ አስተዳደር ሆና ተዋቅራ ነበር። 1983 በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት አሰብን አሳማኝ ባልሆነ ፣ህጋዊ አሰራርን ባለተከተለ ፣እና ይህንን የሚያህል ግዙፍ ህዝብ ከኖረበት የባህር ደጃፍ በመነጠል ወደብ አልባ ሀገር እንድትሆን ፈረደባት፡፡  በወቅቱ የነበረው መንግስትም በፈፀመው ታሪካዊ ስህተት የአሰብ ወደብን ከኤርትራ ጋር ቀላቅሎ እንድትገነጠል አደረገ፡፡

 ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና ስትራቴጂካዊ ፋይዳ

አሰብ በደቡባዊ ቀይ ባሕር ዳርቻ እንደመገኘቷ በአለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ፣ በተለይም የሕንድ ውቅያኖስን ከሜዲትራኒያን ባሕር ጋር በሚያገናኘው የባቢ-ኤል-መንደብ (Bab-el-Mandeb) ወንዝ አቅራቢያ መገኘቷ ከፍተኛ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይሰጣታል።

የአሰብ ወደብ ጥልቅ ባሕር (Deep water port) የመቀበል አቅም ያለው በመሆኑ፣ ግዙፍ የጭነት መርከቦችን ለማስተናገድ ምቹ ነው።

ኤርትራ ከተገነጠለች  በኋላም ቢሆን፣ እስከ ጦርነቱ ዋዜማ  ድረስ ኢትዮጵያ አሰብን እንደ "ነፃ ወደብ" (Free Port) ትጠቀም ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ በራሷ ብር (Birr) የምትገበያይበትና የራሷ ጉምሩክ ቢሮ በአሰብ የነበረበት ሁኔታ ነበር።

አሰብ የዓፋር ሕዝብ አሰፋፈር አካል ናት። አሰብ የአፋሮች መኖርያ ናት፡፡ 90 በመቶ የሚሆኑት አፋሮች ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ስለሆነም አሰብ ኢትዮጵያ ዓፋሮች (የቀይ ባህር ዓፋሮች ተብለው የሚጠሩት) የባህልና የንግድ ማዕከል ነች።

እስከ ኤርትራ  መገንጠል ድረስ በአሰብ ከተማ የሚኖረው ሕዝብ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ (የተለያዩ ብሄረሰቦች ስብጥር ያለበት) ነበር። ወደቡን ተከትሎ የተፈጠሩ ስራዎች፣ ሆቴሎች እና የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያውያን የሚመሩ ነበሩ። ይህ "የሕዝብ ለሕዝብ" ትስስር አሁንም ድረስ በብዙዎች ዘንድ እንደ ትልቅ ትውስታ ይነሳል።

የአሰብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የብሄራዊ ጥቅም (National Interest) ቀዳሚ አጀንዳ የሚሆንባቸው ምክንያቶች አሉ፡-

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለጅቡቲ ወደብ በቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ትከፍላለች። አሰብን መጠቀም መቻል ይህንን ከፍተኛ ወጪ ከመቀነሱም በላይ፣ የአገሪቱን ምርቶች በአለም ገበያ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል። ወደብ አልባ መሆን ማለት "የታሰረ ኢኮኖሚ" ማለት ነው።

አንድ አገር በአንድ የባሕር በር ላይ ብቻ ጥገኝ መሆኗ ለደህንነቷ አስጊ ነው። በባለወደቡ የሚፈጠር ማንኛውም  አለመረጋጋት ወይንም ቀጠናዊ ለውጥ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊጎዳ ይችላል። አሰብ አማራጭ መሆኗ ለኢትዮጵያ የስትራቴጂካዊ በራስ መተማመን (Strategic Autonomy) ይሰጣታል።

 የኢትዮጵያ መንግስት የዘመናት የህዝቡን ብሶትና መብሰልስል ማዕከል የሆነውን የወደብ ጥያቄ ከተቀበረበት ፣በአደባባይ ማውራት ከማይቻልበት ሁኔታ አውጥቶ "የባሕር በር" አስፈላጊነትን በግልፅና በይፋ እያነሳ ይገኛል። የአሰብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወደቦችንም ለመጠቀም በአለም አቀፍ መድረኮች ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም በሙሉ ልብ ጥያቄውን እያቀረበ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የተፈፀመውን ኢፍትሐዊ ድርጊት አለም እንዲገነዘብና ይህንን ታላቅ ሕዝብ ከየብስ እስረኝነት ለማላቀቅ ቁርጠኝነቱንም በዓለም አደባባይ ፊት በመቆም አረጋግጧል፡፡

የዚህ ጥያቄ ምለሽ በትውልዱ እጅ ነው!! ኢትዮጵያን ከወደብ ነጥሎ ለዘልዓለም ማኖር እንማይቻል ጠላትም ወዳጅም ያውቀዋል፡፡ ለዚህ መፍትሄ በጋራ መስራትና ለመፍትሔ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡

ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ ወደነበረችበት የባህር ዳርቻዎች መጠጋቷ የማይቀር ጉዳይ ነው!! አሰብ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን የህልውና እና የብልጽግና መሠረት ነው። የወደቡ ልማትና የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ፣ የአፍሪካ ቀንድ የንግድና የሰላም ማዕከል የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።

ይህንን ፅሁፍ ለማዘጋጀት የዶክተር ያዕቆብ ሀይለማርያም አሰብ የማናት?

የአምባሳደር ዘውዴ ረታ የኤርትራ ጉዳይ

አሰብና አካባቢዋ" — ደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴ

"The Ethiopian Borderlands" — Richard Pankhurst:

"ኤርትራና ኢትዮጵያ" — ተክለጻድቅ መኩሪያ እና ሌሎችም መጣጥፎች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

አዶኒያስ ወ/አረጋይ