Search

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፍትሕ ሚኒስቴር በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

ማክሰኞ መጋቢት 15, 2018 230

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
በተመሳሳይ የፍትሕ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን ተጎጂዎችን ለማቋቋም የሚውል የ3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የ100 ኩንታል ዱቄት ድጋፍ አድርጓል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አርባ ምንጭ ከተማ በመገኘት ድጋፍን ባስረከቡበት ወቅት፣ የሰላም ተምሳሌት በሆነው የጋሞ ህዝብ ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል፡፡
የተደረገው የንዘብ ድጋፍም ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
መሰል አስቸጋሪ ጊዜያትን በጋራ በመቆም በጽናት መሻገር እንደሚገባ የጠቀሱት ዋና አፈ ጉባኤው፣ መንግሥት ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በቀጣይም ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ የሕዝብ ተቋም የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ላደረገው አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል።
ይህ ድጋፍ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ለተያዘው የረጅም ጊዜ ዕቅድ ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
አክለውም እስከ አሁን ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በክልሉ መንግሥት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተመስገን ተስፋዬ