የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የታለመውን የ"አዲስ መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት የልደታ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍን በዛሬው ዕለት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ማዕከሉ የ20 ተቋማትን 112 የተለያዩ አገልግሎቶች በ69 የአገልግሎት መስኮቶች ለተገልጋዮች ያቀርባል። በተጨማሪም 22 ተቋማትን በዲጂታል በይነ-መረብ አስተሳስሯል።
ይህም ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ የነበረውን አሠራር በማስቀረት የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃትን፣ ተደራሽነትን እና የዜጎችን እርካታ ከማሻሻሉም ባለፈ፣ ተገልጋዩ ለጉዳዩ የሚያጠፋውን ጊዜ፣ ገንዘብ እና እንግልት በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረግ ያስችላል።
ይህ አዲስ ማዕከል በከተማዋ ደረጃ ሦስተኛው የ"አዲስ መሶብ" አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፍ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ከተንዛዛ ቢሮክራሲ ለማላቀቅና ለሕዝቡ የሚመጥን የቴክኖሎጂ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ የገባውን ቃል በተግባር እያሳየ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን ከእንግልትና ከብልሹ አሠራር ሙሉ በሙሉ ለማውጣት የተደረጉ ጥረቶች በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ባለመሆናቸው ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት የግድ ሆኗል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከመሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ጋር በተያያዘ እየተከናወነ ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ፣ የነበሩ የሕዝብ ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችን በአመርቂ ሁኔታ እየመለሰ ይገኛል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፣ ቀሪዎቹን ተመሳሳይ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ አጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ሌት ከቀን እየተሠራ ይገኛል።
ይህ የዲጂታል አገልግሎት ሽግግር ነዋሪዎች ያለምንም እንግልትና የሙስና ስጋት የሚፈልጉትን የመንግሥት አገልግሎት በአጭር ጊዜና በአንድ ማዕከል እንዲያገኙ የሚያስችል ትልቅ ተስፋ ነው።
በይመር አደም