Search

የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በጋሞ ዞን ለተጎዱ ወገኖች የ2.1 ሚሊዮን ብር የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች

ማክሰኞ መጋቢት 15, 2018 58

በጋሞ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለመደገፍ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ቀጣናዎች በጋራ በመሆን የ2.1 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አበርክተዋል።
የቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአርባ ምንጭ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ለዞኑ አስተዳደር ያስረከቡ ሲሆን፣ ይህም በወቅቱ ለተጎዱ ወገኖች ያለውን አጋርነት የሚያሳይ ተግባር ሆኗል።
የቤተክርስቲያኗ ዋና ጸሐፊ ስምኦን ሙላት (ዶ/ር) በደረሰው ተፈጥሯዊ አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፣ "ከሚያዝኑ ጋር ማዘን" የሃይማኖታዊ አስተምህሮ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን የተደረገው ምግብ ነክ ድጋፍ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም ቀጣናዎችን በማስተባበር ተጨማሪ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር)፣ ቤተክርስቲያኗና ቀጣናዎች በጋራ በመሆን ላሳዩት ሰብዓዊነት ምስጋና አቅርበዋል።
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ቤተ እምነቶች፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተጎጂዎችን ለማቋቋም በጋራ መቆማቸው ትልቅ ብርታት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በአደጋው ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን፣ ሴቶችንና ነፍሰ ጡር እናቶችን በልዩ ሁኔታ ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
በተመስገን ተስፋዬ