Search

ምንም እንኳ የዓለም አቀፍ አቅርቦት ቢፈታተነንም፣ በበልግ ዝናብ ውጤታማ መሆን ይቻላል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ ር)

ማክሰኞ መጋቢት 15, 2018 67

የዓለም አቀፍ የነዳጅና የማዳበሪያ አቅርቦት ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ጸጋዎችና ወቅታዊ ዝናብን በአግባቡ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባታል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ አርሶ አደሩ የበልግ ወቅትን ለላቀ ምርታማነት እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘንድሮው የበልግ ወቅት ቢያንስ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ከተቻለ ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
በአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ቢዘራና በሄክታር በአማካይ 40 ኩንታል ቢገኝ፣ በአጠቃላይ 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማምረት እንደሚቻል በማብራሪያቸው አመላክተዋል።
"የበልግን ዕድል ያበላሸ ክረምትም ያመልጠዋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ መሬቱን አርሶና አለስልሶ ዝናብን እንዲጠባበቅ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሀገራችን ያሏትን የተፈጥሮ ጸጋዎች አውቆ መጠቀም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የፓልም ዛፎችንና የፍልውኃ ጸጋዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ በመግለጽ፤ "ሌሎች ሀገራት ከፍተኛ መከራ አይተው የሚተክሏቸውን የፓልም ዛፎች እኛ በተፈጥሮ በነፃ አግኝተናል፤ እኛ ያደረግነው ጎጆ ቀልሰን ተፈጥሮን ከውበት ጋር ማስማማት ነው" ብለዋል።
ሀገራችን ያሏትን የተፈጥሮ ጸጋዎችና ወቅታዊ የዝናብ ዑደቶች በቴክኖሎጂና በትጋት ማገዝ ከተቻለ፣ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎችን ተቋቁሞ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
ይህ የልማት ጥሪም አርሶ አደሩንና የዘርፉን ባለሙያዎች ለላቀ ሥራ የሚያነሳሳ ተደርጎ ተወስዷል።
በሃይማኖት ከበደ