ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የጀመረችው እንቅስቃሴ የረጅም ጊዜ የኃይል ዋስትና ለማረጋገጥ ያለመ ስትራቴጂካዊ ውሳኔ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ የነዳጅ መኪናዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ የተያዘው አቅጣጫ መጀመሪያ ላይ ቅሬታዎች ቢነሱበትም፣ ዓለም አቀፋዊ የነዳጅ ዋጋ መዋዥቅና የጂኦፖለቲካዊ ግጭቶች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ለመቋቋም ብቸኛው አማራጭ ነው።
ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች ሀገር አለመሆኗን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የነዳጅ ዋጋ በጨመረ ቁጥር የሚከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በሀገር ውስጥ የሚመረተውን የታዳሽ ኃይል መጠቀም የኃይል ሉዓላዊነትን እንደሚያረጋግጥ አብራርተዋል።
"በዋጋ ደረጃ የነዳጅና የኤሌክትሪክ ወጪ እኩል ቢሆን እንኳ፣ የኤሌክትሪክ መኪና ተመራጭ ነው፤ ምክንያቱም ኃይሉን እዚሁ ሀገር ውስጥ ስለምናመርት እንደ ነዳጅ 'ተዘጋብኝ' የሚል ስጋት አይኖርም" በማለት የችግሩን አሳሳቢነትና የመፍትሔውን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል።
ወደ ኤሌክትሪክ መኪና የሚደረገው ሽግግር ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለነዳጅ ግዢ ከመስጠት የሚታደግ ከመሆኑም ባለፈ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለዜጎች የኑሮ ጫና መቀነስ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
መኪናዎቹ ጪስና ድምፅ የሌላቸው መሆኑ እንዲሁም የማንቀሳቀሻ ወጪያቸው እጅግ አነስተኛ መሆኑ ለሀገርም ሆነ ለተጠቃሚው ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በመሆኑም ይህ ሽግግር ድንገተኛ ዓለም አቀፍ ቀውሶች በዜጎች ሕይወትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ለመቀነስ የተመረጠ ብልህ ስትራቴጂካዊ አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBC #Ethiopia #PMAbiyAhmed #ElectricVehicles #EnergySecurity #GreenLegacy