የኮሪደር ልማት የከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የነዋሪዎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ድርብርብ ዓላማ ያለው ግዙፍ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ማንኛውም የልማት ሥራ ግልጽ ግብ ሊኖረው እንደሚገባ በመጥቀስ፣ የኮሪደር ልማት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ግቦችን በአንድነት አቀናጅቶ የያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ በግንባታ ወቅትና ከግንባታ በኋላ ተከታታይነት ያለው የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ለወጣት መሐንዲሶች ትልቅ የተግባር ልምድ መጋሪያ ሆኖ ማገልገሉን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲ ከሚገኘው የንድፈ-ሐሳብ እውቀት ባለፈ ወጣቶች ከፍተኛ የተግባራዊ እውቀት እንዲቀስሙ ማስቻሉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአዲስ አበባ ልምድ ያገኙ ወጣቶች አሁን ላይ በክልል ከተሞች አስገራሚ የዲዛይንና የግንባታ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱ አንዱ አካል የሆነው የቤት ግንባታ፣ በሀገሪቱ የነበረውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ በከፍተኛ ፍጥነት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለመገንባት ማስቻሉን አንስተዋል።
ልማቱ ይዞታዎችን በመለየትና ለተገቢው ዓላማ በማዋል፣ ለኑሮ የማይመቹና በላስቲክ የተሠሩ ቤቶች በዘመናዊና ደረጃቸውን በጠበቁ ሕንፃዎች እንዲተኩ እያደረገ መሆኑም አብራርተዋል።
በተጨማሪም የመንገድ፣ የመብራትና የእግረኛ መንገዶች መሻሻል በኮሪደሩ አቅራቢያ ያሉ የቤትና የሕንፃ ዋጋዎች እጅግ እንዲጨምሩ በማድረጉ፣ ባለሀብቶች በልበ ሙሉነት በዘርፉ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።
ልማቱ አማራጭ መንገዶችን በመፍጠርና የነበሩትን በማስፋት፣ ቀደም ሲል የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ ደረጃ መቅረፉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የመኪናና የእግረኛ መንገዶች ተለይተው በመሠራታቸው፣ ነዋሪዎች ሳይጉላሉ በፈጠነ ጊዜ ወደሚፈልጉት ቦታ መድረስ እንዲችሉ ማድረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።
በመሀመድ ፊጣሞ
#EthiopianBroadcastingCorporation #Ethiopia #CorridorDevelopment #UrbanRenewal #PMAbiyAhmed