የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በታሪካዊቷ ፒያሳ ለወርቅ ንግድ ሱቆች አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ የተገነባውን ዘመናዊ የንግድ ሕንፃ (ጎልድ ሞል) ዛሬ አስመርቋል።
የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትርና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ እንዲሁም በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) አማካኝነት ተከናውኗል።
የ50 ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ ስኬታማ ተግባራት እያከበረ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፣ ይህንን ዘመናዊ የንግድ ማዕከል ለምረቃ ማብቃቱ ለንግዱ ማህበረሰብ በተለይም ለወርቅ ነጋዴዎች ትልቅ የምስራች ሆኗል።
ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ ያለበትን የሥራ ብቃት እና የሽግግር ወቅት በማሳየት፣ ለንግድ ግልጋሎት የሚውሉ ዘመናዊ ሕንፃዎችን በብዛት በመገንባት የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ በትጋት እየሠራ ይገኛል።
ይህ በፒያሳ አዲስ ገጽታ ላይ የተገነባው የንግድ ሞል፣ የከተማዋን የኮሪደር ልማት ተከትሎ ለሚመጡ የንግድ ፍላጎቶች ምላሽ የሚሰጥና ለአካባቢው ውበት የጨመረ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በኢዮቤልዩ ዓመቱ እያስመዘገበ ያለው ይህ ስኬት፣ ተቋሙ በሀገር ግንባታና በከተሞች ዘመናዊነት ላይ ያለውን ቁልፍ ሚና ዳግም ያረጋገጠበት ነው።
ሃብታሙ ተክለሥላሴ