Search

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ባለሙያዎችን አስመረቀ

ቅዳሜ መጋቢት 19, 2018 115

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 255 ተማሪዎች ዛሬ በደመቀ ሁኔታ አስመርቋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ተቋሙ እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ በጤናው ዘርፍ ብቁና ባለሙያዎችን ለማፍራት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ የጤና ችግሮች እየተፈተነች መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያካበቱትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የማኅበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ አሳስበዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ተመራቂዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋዎች መሆናቸውን በመግለጽ፤ ሙያና ሥነ-ምግባርን በማዋሃድ ማኅበረሰቡን በቅንነት እንዲያገለግሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ በበኩላቸው፤ ጤናማና አምራች ማኅበረሰብ ለመፍጠር የጤና ባለሙያዎች ሚና የማይተካ መሆኑን ገልጸው፤ ተመራቂዎች ዘመኑን የዋጀ ክህሎት በየጊዜው በመቅሰም በሀገራችን ዘላቂና የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው 255 ተማሪዎች መካከል 190ዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 52ቱ በስፔሻሊቲ እንዲሁም 13ቱ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፤ ከተመራቂዎቹ መካከልም 99ኙ ሴቶችና 156ቱ ወንዶች መሆናቸው ታውቋል።
በሳሙኤል ወርቃአየሁ