Search

ከእርዳታ ጥገኝነት ወደ ምግብ ሉዓላዊነት የተደረገ ታሪካዊ ሽግግር በስንዴ ልማት

ቅዳሜ መጋቢት 19, 2018 128

ባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከተመዘገቡት ደማቅ ስኬቶች መካከል የስንዴ ልማት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
ኢትዮጵያ ለፍጆታ የሚሆን ስንዴን ከውጭ ለማስገባት በዓመት 1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ታወጣ የነበረበትን ታሪክ በመቀየር፣ ዛሬ ላይ ራሷን ችላ ምርቷን ለዓለም ገበያ መላክ የጀመረችበት አዲስ የከፍታ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ለዚህ ተአምራዊ ስኬት ዋነኛው ምክንያት "የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት" ስትራቴጂ ሲሆን፣ ይህም የምርት መጠኑ ከእጥፍ በላይ እንዲያድግና መሬትን በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሏል።
በ2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ በምግብ ራሷን የመቻል ግቧን በተግባር ማሳካቷን ለዓለም ያበሰረችበት ታላቅ ክስተት ነበር።
ይህ ስኬት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አይነት ዓለም አቀፍ ቀውሶች በሀገር ውስጥ የዳቦና የዱቄት አቅርቦት ላይ የከፋ ችግር እንዳያመጡ ትልቅ መከላከያ ሆኗል።
በተጨማሪም ዓመታዊ የስንዴ ምርትን ወደ 231 ሚሊዮን ኩንታል በማድረስ የስንዴ ገቢ ምርትን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት ወደ ውጭ የመላክ አቅም ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ስኬት እንደ ዓለም አቀፉ የግብርና እና የምግብ ድርጅት (FAO) ባሉ ተቋማት እውቅናን ያገኘ ሲሆን፣ አርሶ አደሩንም ከቤት ፍጆታ ባለፈ ወደ ገበያ መርና ዘመናዊ የሜካናይዜሽን ግብርና ተጠቃሚነት አሸጋግሮታል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ከኢኮኖሚ ባለፈ የሀገርን የፖለቲካ ነፃነትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም የሚያሳድግ በመሆኑ፣ ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በ2030 መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ለመሆን ለያዘችው ራዕይ አንድ ስኬት ተደርጎ የሚጠቀስ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ይህ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተገኘ አስገራሚ ለውጥ ኢትዮጵያ እየገነባች ላለው የማይበገር ኢኮኖሚ አንዱ አበርክቶ ያለው ሲሆን በፈተናዎች አልፋ የጸናች ኢትዮጵያን የመፍጠር ህልም እየተሳካ እንደሆነ ማሳያ ሆኗል።
በመሀመድ ፊጣሞ