Search

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዕውቅናና አድናቆት የተቸራት ለምንድን ነው?

ሰኞ መጋቢት 21, 2018 131

በአዲስ አበባ በስኬት የተጠናቀቀው "ኢንቨስት በኢትዮጵያ 2026" ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ የ13.1 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን በማካሄድ የዓለምን ትኩረት ስባለች።
ይህ ድንቅ ውጤት እንደ ሮይተርስ፣ ብሉምበርግ እና ዥንዋ ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች የዘገባዎቻቸው መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።
እንደ ብሉምበርግ ዘገባ፣ የተፈረሙት ስምምነቶች የታዳሽ ኃይል፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የሪል ስቴት፣ የማዕድን እና የ"አረንጓዴ አሞኒያ" ስትራቴጂካዊ ዘርፎችን ያካተቱ ናቸው።
ሮይተርስ በበኩሉ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) በመሳብ ለ130 ሚሊዮን ሕዝቧ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የምታደርገው እንቅስቃሴ ለቀጣናው አርአያ የሚሆን መሆኑን አሞካሽቷል።
የኢኮኖሚ መረጃ ምንጭ የሆነው ቢር ሜትሪክስ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መጀመሪያ ካቀደው 2.4 ቢሊዮን ዶላር አንጻር የተመዘገበው የ13.1 ቢሊዮን ዶላር ውጤት ከተጠበቀው በላይና ከፍተኛ የመደራደር አቅም ያሳየ መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ሕብረት በ"ግሎባል ጌትዌይ" ስትራቴጂው አማካኝነት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ያለውን ዝግጁነት በመግለጽ በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በንቃት እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቋል።
ይህ ዓለም አቀፍ ሽፋን ያገኘው የ2026 የኢንቨስትመንት ፎረም፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ብልጽግና ያላትን ቁልፍ ሚና ዳግም ያረጋገጠችበትና ዓለምን ያስደመመችበት ታላቅ መድረክ ሆኖ ተመዝግቧል።
በመሀመድ ፊጣሞ