Search

ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ፦ አዲሱ የኢትዮጵያ ቁልፍ የዕድገት ምሰሶ

ማክሰኞ መጋቢት 22, 2018 150

ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድር እና በአየር ንብረት ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በልዩ ሁኔታ ከታደሉ ጥቂት ሀገራት መካከል ትመደባለች። እንደዚህ ዓይነቱን ስጦታ የታደሉት ሀገራት ውበታቸውን ለዓለም በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ሀብታቸው ተዝቆ የማያልቅ በረከት ያፍሳሉ።

ሀገራችን ግን "ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ" ተብሎ የሚጠራውን የቱሪዝም ዘርፍ ለረጅም ዘመናት እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሳትቆጥረው ቆይታለች።

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ እና የታሪክ ሀብት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም ለመለወጥ የሚያስችል ስልታዊ አመራር ባለመኖሩ፣ ጎብኚዎች በጥቂት ነባር መዳረሻዎች ላይ ብቻ ተወስነው እና የቱሪዝም አማራጮች እጅግ ውስን ሆነው ቆይተዋል። ይህ ሁኔታ ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ፣ የሥራ ዕድል እና ዓለም አቀፍ ገጽታ ግንባታ ለበርካታ ዓመታት እንድታጣ አድርጓታል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በመጋቢት ለውጥ ማግስት በተቀረጸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት፣ ቱሪዝም ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ ተለይቶ በመቀመጡ ዘርፉ ወደ ተጨባጭ የዕድገት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ይህ በለውጡ ዘመን የመጣው ስር ነቀል ሽግግር በወረቀት ላይ የሰፈረ ዕቅድ ብቻ ሳይሆን፣ በመሬት ላይ በሚታዩ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች እና በአዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተረጋገጠ ይገኛል። በተለይም በአዲስ አበባ የተተገበሩት "ገበታ ለሸገር" ፕሮጀክቶች ከተማዋን ከምቹ መኖሪያነት ባለፈ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መስህብ ማዕከል እንድትሆን አድርገዋታል። እንደ አንድነት፣ እንጦጦ እና ወዳጅነት ያሉ ዘመናዊ ፓርኮች እንዲሁም የዓድዋ ድል መታሰቢያ የከተማዋን የታሪክ እና የተፈጥሮ ውበት በማቀናጀት አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል። እነዚህ መዳረሻዎች በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን እየሳቡ የሚገኙ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ያለውን የቱሪስት የቆይታ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገውታል።

በተጨማሪም አዲስ አበባን ይበልጥ ምቹ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን "አፍሪካ አዲስ ፊት" በማድረግ ለስፖርት እና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል። በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በዓመት 150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን እያዘጋጀች ትገኛለች። የመንግሥት የቱሪዝም ልማት ፖሊሲ  በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን የሀገራችንን ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሀብቶች በየክልሉ ለማልማት "ገበታ ለሀገር" እና "ለትውልድ" የተሰኙ ግዙፍ መርሐ ግብሮችን ተግባራዊ አድርጓል። በእነዚህ መርሐ ግብሮች አማካኝነት እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ ያሉ አካባቢዎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መዳረሻዎች ተገንብተውባቸዋል። 

በቅርቡ የተመረቁት ሸበሌ ሪዞርት፣ ደምቢ ኢኮ ሎጅ፣ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት እና ኒዒን ፓልም ሎጅ የጉዞው ስኬት ማሳያዎች ሲሆኑ፣ ጎንደርን ወደ ቀድሞ ልዕልናዋ የመለሰውና እንደ አባ ጂፋር ቤተ መንግሥት ያሉ ቅርሶችን የታደሰውም ይኸው ስልታዊ ፖሊሲ ነው። የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለሕዝብ ክፍት መሆንም ለሀገራችን ሌላኛው የኩራት ምንጭ ሆኗል። የዘርፉ ሽግግር በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ዕውቅናን እያገኘ የመጣ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ባሮሜትር መረጃ መሠረት ሀገራችን 2025 በዓለም አቀፍ የቱሪስቶች ፍሰት 15 በመቶ ዕድገት በማሳየት ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል ተመድባለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚከተለው የቆይታ ቱሪዝም ስትራቴጂም በአዲስ አበባ በኩል ወደ ሌሎች ሀገራት የሚጓዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞችን ወደ ቱሪስትነት በመቀየር ለሀገራችን የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው። አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ ሀገራችን 700 ሺህ በላይ ቱሪስቶችን አስተናግዳ ከዘርፉ 2.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች። የሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ መጻኢ ተስፋ እጅግ ብሩህ መሆኑን አሁን ከታየው ውጤት መረዳት ይቻላል።

በቢሾፍቱ አካባቢ የሚገነባው እና በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዘርፉ እንዲጎመራ ከሚያደርጉት አስቻይ ሁኔታዎች መካከል ይመደባል።

በተለይም የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የጮቄ ተራራን፣ ወንጪን እና ሌጲስን "ምርጥ የቱሪስት መንደሮች" በማለት ዕውቅና መስጠቱ ሀገራችን ለዘላቂ እና ለማኅበረሰብ ተኮር ቱሪዝም የምትከተለው አቅጣጫ ውጤታማ መሆኑን ያረጋግጣል።

ሀገራችን አቧራ የለበሱ ታሪኮቿን በማደስ እና ነባር ሥልጣኔዎቿን ለዓለም በማሳየት የጀመረችው ጉዞ፣ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የብልጽግናችን ዋነኛው የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ እንዲያገለግል የማድረግ አቅም እንዳለው በተግባር አስመስክራለች።

በለሚ ታደሰ

#Ethiopia #LandOfOrigins #TourismTransformation #EcoTourism #EthiopianAirlines