Search

የዲፕሎማሲው ክንድ፦ ከተፅዕኖ ተቀባይነት ወደ አህጉራዊ መሪነት!

ሓሙስ መጋቢት 24, 2018 141

የዓለም ፖለቲካ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተለዋወጠ ይገኛል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በኋላ የነበረው የአንድ ዋልታ የበላይነት እያከተመ፣ የባለብዙ ዋልታ ሥርዓት እየመጣ ነው።

ይህ የዓለም ሥርዓታዊ ለውጥ አዳዲስ ዕድሎችን እና ሥጋቶችን ይዞ የመጣ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ፈተናዎችን በመሻገር ብቻ ሳይሆን፣ አያሌ የዲፕሎማሲ ድሎችን በማስመዝገብ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ክብሯን ማስከበር ችላለች።

ሀገራችን የተከተለችው "የመደመር" እሳቤ የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ፣ ፉክክር እና ትብብርን የሚያስታርቅ ፍልስፍናን በማቅረብ፣ የውጭ ግንኙነታችንን በአዲስ መልክ ቀይሮታል።

1. ከከበባ ወደ ቀጣናዊ የትብብር ማዕከልነት

·      ትናንት፦ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የነበራት ሚና እና ከሀገራት ጋር የነበራት ግንኙነት "የምትፈራ" እንድትሆን ከማድረግ ባሻገር፣ የቀጣናው ሀገራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስስ፣ አጭር ርቀት እና ወደ ውጭ ተመልካች እንዲሆን የሚያደርግ ሁኔታ ነበር።

·      ዛሬ፦ "ቅድሚያ ለጎረቤት" በሚለው ፖሊሲ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ዋነኛ መሠረት ሆኗል።

የኢኮኖሚ ጥገኝነትን ወደ እኩልነት እና የጋራ ብልጽግና ለመቀየር፣ በመሠረተ ልማት፣ በመንገድ ግንባታ እና በታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ትሥሥርን በማጠናከር ላይ እንገኛለን።

ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋነኛ ገዢዎች ሲሆኑ፣ ከታንዛኒያ ጋር እየተከናወነ ያለው የሙከራ ፕሮጀክትም የኃይል ሽያጩ ይበልጥ እንደሚሰፋ ማሳያ ነው።

ይህ አካሄድ ኢትዮጵያን ለቀጣናው የዴሞክራሲ፣ የሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም የብልጽግና ተምሳሌት እና መሪ እንድትሆን አስችሏታል።

2. የባሕር በር ጥያቄ፦ ከዝምታ ወደ ዓለም አቀፍ አጀንዳነት

·       ትናንት፦ ኢትዮጵያ በባሕር በር የመጠቀም መብቷን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በታሪክ ሂደት ማጣቷ፣ የመልክዓ-ምድር እስረኛ እንድትሆን እና የኢኮኖሚ ፍላጎቶቿ እንዲገደቡ አድርጎ ቆይቷል። የባሕር በር ጥያቄአችን ለሦስት ዐሥርተ ዓመታት ታፍኖ ኖሯል።

·       ዛሬ፦ ለዘመናት ታፍኖ የቆየው የፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት እና ተጠቃሚነት ጥያቄ፣ በጥበብ በተሞላው የዲፕሎማሲ አመራር ከሕዝባችን አልፎ ዓለም ዕውቅና እንዲሰጠው ማድረግ ተችሏል።

ዘላቂ፣ አስተማማኝ እና በቂ የባሕር በር የማግኘት ፍትሐዊ ጥያቄያችንን በሰጥቶ-መቀበል (Win-Win) መርሕ፣ በውይይት፣ በድርድር እና በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረት በሰላማዊ መንገዶች ለማሳካት በጽኑ እየሠራን ነው።

3. የብሪክስ (BRICS) አባልነት እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ

  • ትናንት፦ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ፖለቲካዊ እና የደኅንነት ግቦችን ብቻ ያማከለ፣ ከብድር እና ዕርዳታ ድጋፎች አንጻር ብቻ የሚመዘን አጭር ርቀት ያለው አካሄድ ነበር።

 ዛሬ፦ የማይደራደር ሉዓላዊነትን ይዘን የዓለምን ግዙፍ የኢኮኖሚ ጥምረት 'ብሪክስ'ን (BRICS) ሙሉ አባል ሆነናል። ይህ አባልነት ለሀገራችን ትልቅ የኢንቨስትመንት ምንጭ እንዲሁም ለምርቶቻችን ሰፊ ገበያን የሚፈጥር ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መድረክ ያላትን ተሰሚነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ሀገራችን በአፍሪካ ኅብረት ሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል መሆኗ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያችንን ስኬት ያሳያል።

4. ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፦ ከስጋትነት ወደ አጋርነት

·      ትናንት፦ ዳያስፖራው በአብዛኛው እንደ ስጋት ይታይ የነበረበት እና የዜጎች መብት እና ደኅንነት በበቂ ሁኔታ የማይጠበቅበት ጊዜ ነበር።

·      ዛሬ፦ ዳያስፖራውን እንደ ቤተሰብ በመቁጠር፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ምንጭ ፍሰት ጉልህ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ዜጎቻችን መብት እና ደኅንነት መከበር ከበርካታ ሀገራት ጋር የሥራ ስምሪት ስምምነቶች ተፈርመዋል። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት በመመለስ፣ ክብራቸውን የማስጠበቅ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም በተሳካ ሁኔታ ተፈጽሟል።

5. የሕዳሴ ግድብ፦ የዲፕሎማሲያችን እና የብሔራዊ ኩራታችን አርማ

·      ትናንት፦ የሕዳሴ ግድብ ለብክነት እና ስብራት ተዳርጎ ከነበረበት ውድቀት በማንሣት፣ የውጭ ጫናዎች እና ሴራዎች በብዛት የሚስተዋሉበት ፕሮጀክት ነበር።

·      ዛሬ፦ የሕዳሴው ግድብ የፕሮጀክት አመራር ክፍተቶችን በማረም እና የዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎዎችን በማጠናከር፣ ግድቡ በስኬት እንዲጠናቀቅ ተደርጓል።

ጫናዎችን በመቋቋም፣ በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ እና "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚል መርሕ፣ ጉዳዩ በሦስትዮሽ ድርድር እንዲታይ ማድረግ ተችሏል። የዓባይ ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ፣ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ታሪካዊ ሚና ተጫውተናል።

በአጠቃላይ፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተጓዝንበት መንገድ በድሎች የታጀበ፣ በፈተናዎች የጸና እና በተስፋ የተሞላ ነው። ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን ከርዕዮተ ዓለም እስረኛነት ነፃ በማውጣት፣ ሚዛናዊ፣ ሀገር-በቀል እና የዜጎችን ጥቅም ያስቀደመ ዲፕሎማሲ በመከተል፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት እና የጂኦ-ፖለቲካ ተጽዕኖዋን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጋለች።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ